‹‹እኛ ላይ ከደረሰው ጉዳት ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ይበልጣል!›› የዘ-ሀበሻ ድረ-ገፅ ባለቤት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ Image copyright ANADOLU AGENCY

የኢትዮጵያ መንግሥት ስም እና ረቂቅ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተገዳዳሪ የዜና ተቋማት ድረ-ገጾችን የማፈን ልማድ ለዓመታት በቁርኝት ተራምደዋል፡፡ በዓመታት ውስጥ Deep Packet Inspection (DPI) በተሰኘው ልዩ ማጥለያ ዘዴ እየተጠለፉ ለጎብኝዎች ከመድረስ የታገዱ ድረ-ገፆች ብዛት ከፍተኛ ነው፡፡

ቀዳሚ ዓመታትን ትተን ከሦስት ዓመታት በፊት በመላው ሀገሪቱ የተነሳውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ 16 የዜና ተቋማት በሀገር ውስጥ እንዳይታዩ መታፈናቸውን በወቅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ ተቋም አጋልጧል፡፡

በመሰል ርምጃዎቹ በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ሲብጠለጠል የሰነበተው የኢትዮጵያ መንግሥት ‹ታሪክ ቀያሪ› ስለመሆኑ የተጠቀሰ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻዎች

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ላይ ይፋ እንዳደረጉት ሀገር ውስጥ እንዳይጎበኙ ታፍነው የነበሩ ከ250 በላይ ድረ-ገጾች ክልከላው ተነስቶላቸዋል፡፡

መታፈን ማንን ጎዳ?

ሄኖክ ዓለማየሁ ደገፉ አሜሪካን የስደት ዘመን መጠለያ ካደረጉ ጋዜጠኞች እና አሳታሚዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በፖለቲካ፣ መዝናኛ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ድረ-ገጽ አስተዋወቀ፡፡

መጠሪያው "ዘ-ሀበሻ" የሆነው ይሄ ድረ-ገጽ በመንግሥት እጅ ውስጥ በነበሩ የዜና ተቋማት ተመሳሳይ ዘገባ ተሰላችቶ ለነበረው ‹‹ዲያስፖራ›› እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ ሆነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን "ዘ-ሀበሻ" ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበብ እግድ እንደተጣለበት አዘጋጆቹ አወቁ፡፡

‹‹እኛ ላይ ከደረሰው ጉዳት ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ይበልጣል!›› ይላል ሄኖክ፣አንባቢያን ከእገዳው ሾልከው ድረ-ገጹን ለመጎብኘት የተለያዩ መተላለፊያ ሶፍትዌሮችን ለማግኘት ለወጪ እና ለሰዓት ብክነት መዳረጋቸውን በማስታወስ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ፕሮጀክት መሥራች ሶሊያና ሽመልስ በሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ደረሱ የምትላቸውን ጥቃቶች በየመድረኩ ስታሰማ ባጅታለች፡፡

ለእርሷ የኢትዮጵያ መንግሥት ድረ-ገጾችን የማፈን ርምጃ የመጀመሪያ ጉዳቱ አማራጭ ሐሳቦች የሚደመጡበትን ቀዳዳ መድፈኑ ነው፡፡

"(ርምጃው) የመረጃ ፍሰቱ የተገደበ እንዲሆን፣ ሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ትርክት መንግሥት በሚፈልገው አንድ መንገድ ብቻ ቅርፅ እንዲይዝ አድርጎታል፤ ዓላማውም ይሄ ነበር፡፡" በማለት የምታብራራው ሶሊያና መንግሥት ድረ-ገጾችን በመዝጋቱ፣ የሐሳብ ውድድርን በማጥፋት ሕዝቡ ሕይወት ቀያሪ መረጃዎችን የማግኘት መብቱ እንዴት እንደተነፈገ ታወሳለች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እርምጃዎች የት ድረስ?

Image copyright ZEHABESHA

መንግሥት ድረ-ገጾች በሀገር ቤት አንባቢያን ወይንም ተመልካቾች እንዳይታዩ ያደርግ እንደነበር በተዘዋዋሪ መንገድ ማመኑን እንደ አንድ ልዩ ነገር የምታነሳው ሶሊያና የአሁኑ ርምጃ ያለውን ዐብይ ፋይዳ ታነሳሳለች፡፡

ጦማሪ እና የመብት ተሟጋች ሶሊያና ሽመልስ የኢትዮጵያ መንግሥት በድረገጾች ላይ አድርጎት የነበረውን ክልከላ ማንሳቱ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ሕዝቡ እንደሆነ ትጠቁማለች፡፡

ሕዝቡ አንድን ርእሰ ጉዳይ በተለያየ አቅጣጫ የሚተረጉሙ የመገናኛ ብዙኃንን ካለ ገርጋሪ ለመታደም፣ የሚበጀውን ሐሳብ የመምረጥ ዕድሉን እንደሚፈጥርለት ታሰምራለች፡፡

የ"ዘ ሀበሻ" ድረ-ገጽ ባለቤት ሄኖክ አለማየሁ በበኩሉ ከእገዳው መነሳት በተጨማሪ የመንግሥት ባለሥልጣናት መቀመጫቸውን በውጭ ሀገራት ላደረጉ ድረ-ገፆች ምላሽ ያለመስጠት እና መረጃን የመንፈግ አሠራራቸውን እንዲያርሙ ይመክራል።

"የመንግሥት ኃላፊዎች በራቸውን ክፍት ካደረጉ ዘገባዎቻችንን ሚዛናዊ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ እስከ አሁንም ሚዛናዊ አይደሉም ተብለን የምንተችባቸው ምክንያቶች ለ27ዓመታት ለነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ደፍሮ መረጃ የሚሰጥ የመንግሥት ኃላፊ አለመኖሩ ነው፡፡" ይላል ሄኖክ፡፡

የኢትዮጵያን አንገት የሚያስደፋ የፕሬስ ነጻነት እና የጋዜጠኞች ደኅንነት ደረጃ ሲያጋልጡ ከከረሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካካል "ሲፒጄ" አንዱ ነው፡፡

ድርጅቱ ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር የተወሰዱ ርምጃዎችን በአውንታ እንደሚያይ ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡ የድርጅቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አንጄላ ኩዊንታል አክለው መንግሥት ከዚህ ርምጃ በተጨማሪ ሊወስዳቸው ይገባል ያሏቸውን ርምጃዎች አጋርተዋል፡፡

"በ2009 እ.ኤ.አ የወጣው የጸረ-ሽብር ሕግ ፕሬሱን ድምጽ አልባ ለማድረግ በሥራ ላይ ሲውል ቆይቷል፡፡ ይህ ሕግ መከለስ እንዳለበት ከዚህ በፊት በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች በጉዳዩ ላይ እየተወያዩበት መሆኑን ተረድተናል፤ ይሄም አስደስቶናል፡፡" ያሉት የሲፔጃ ባልደረባ፣ በተመሳሳይ የሀገሪቱ የወንጀል ሕግ የተወሰኑ የስም ማጥፋትን የሚመለከቱ አንቀጾች ጋዜጠኞችን ለመጨቆን በሥራ ላይ እንደዋሉ በመግለጽ፣ "በግልጽ አንቀጾች መሻር አለባቸው፡፡" ብለዋል አንጄላ፡፡

'ለአደጋ የተጋለጠው' የኢትዮጵያ ህትመት ሚድያ

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ