ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ወሳኝ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃቸው በ100 ቀናት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ወደ መሪነት መምጣት ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ለውጦች እየተካሄዱ ነው። የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኢኮኖሚውን ነፃ ለማድረግ በሚል በመንሥስት ይዞታ ስር የሆኑትን ቴሌ ኮሙኑኬሽንን፣ አየር መንገድን በከፊል ወደግል ለማዘዋወር ወስኗል።

ከእነዚህ ድርጅቶች በተጨማሪም የኢንደስትሪ መንደሮችን፣ የስኳር ፋብሪካዎችን፣ ሆቴሎችን እና ሌሎች አምራች ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር ተወስኗል።

ይህ ውሳኔ የተወሰነው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱንና የዋጋ ግሽበቱን ለመቋቋም፣ የገቢ ማመንጨት አቅምን ለማጠናከርና የወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ በሚል ነው።

ለዚህ ውሳኔ ሌላኛው ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከፍ በማለቱም እንደሆነ ተነግሯል።

በአሁኑ ሰዓት መንግስት ያጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎችን እየጎዳ መሆኑ ይነገራል።

አበበ መኮንን በአዋሽ መልካሳ የአንድ አነስተኛ መድሀኒት ቤት ሰራተኛ ነው። ባለፉት አራት ወራት ከፍተኛ የሆነ የመድሃኒት እጥረት እንዳለ ይናገራል።

"በርካታ ሰዎች የወባ መድሀኒት ይጠይቁናል፤ ነገር ግን የለንም። በዚህች ከተማ ለአንዳንድ ሕመሞች የሚፈለግ ክንኒም ሆነ መርፌ ማግኘት ከባድ ነው" ይላል።

ሰዎች ከሐኪም የታዘዘላቸውን መድሃኒት ሳይዙ ባዶ እጃቸውን ነው ወደ ቤታቸው የሚመለሱት የሚለው አቶ አበበ በዚህም የተነሳ ሕሙማን ፈውስ ርቋቸው ለመኖር ተገደዋል ይላል።

"የጅምላ አከፋፋዮቹም በመጋዘናቸው ውስጥ ምንም የላቸውም። እነርሱ እያሉት ያለው ዶላር የለም ነው" በማለት ለቢቢሲ ገልጧል።

"175 ብር እንሸጣቸው የነበሩ መድሃኒቶች 900 ብር ገብተዋል፤ ስለዚህም ሰዎች መግዛት አልቻሉም" ሲል ይጨምራል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያካሄዳቸው ኢንቨስትመንቶች በሚል ትላልቅ ማሺነሪዎችንና ቁሳቁሶችን ከዓለምአቀፍ ገበያ ይገዛል፤ እንደ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ ደግሞ ይህ ግዢ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ክምችት እያሟጠጠና ከፍ ያለብድር ውስጥ የከተተ ነው።

የተከፋፈለ ኃሳብ

በኪዊን ማሪ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን የምጣኔ ሐብት ምሁር የሆኑት አቶ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) "መንግስት ገቢ ከማያመነጩ እና የዶላር እጥረቱን ከማይቀርፉ ከእንደዚህ አይነት ትልልቅ ግንባታዎች ራሱን መግታት አለበት" ይላሉ።

መንግስት በቁጥጥሩ ስር ያሉትን ተቋማት ወደ ግል ይዞታ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ ግል አዞራቸዋለሁ ካለ በኋላ በምሁራኑ መካከል አንድ ወጥ አቋም አይታይም ።

የምጣኔ ሐብት ምሁሩ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) እነዚህ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ መዛወራቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተጠቃሚዎች የተሻለ አገልግሎትና ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፤ እንዲሁም ይላሉ ምሁሩ የዋጋውን ግሽበት ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል።

እንደ ዶ/ር ነመራ ከሆነ ግን በአሁኑ ወቅት እነዚህን ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወር ሀገሪቱን ወደባሰ የኢኮኖሚ ቀውስ መግፋት ይሆናል።

"የሀገሪቱ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ በኪራይ ሰብሳቢዎችና በሙሰኞች እጅ ነው የሚገኝው፤ እነዛ ሰዎች ናቸው እነዚህን ድርጅቶች የሚገዙት፤ ይህ ደግሞ በግለሰቦችና ቡድኖች መካከል ያለውን የሀብት ልዩነት ክፍተት ከፍ ያደርገውና ወደ ቀውስ ያመራል። "

በከፍተኛ ሁኔታ በአስመጪና ላኪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኪራይ ሰብሳቢዎችን የሚቆጣጠር መስፈርት መዘርጋት እንዳለበትም ይመክራሉ።

በአዋሽ መልካሳ የኢንተርኔት ካፌ ባለቤት የሆነው ተክለማርያም "ኢንተርኔት ቀርፋፋ ነው። በተደጋጋሚም ይቆራረጣል። አንዳንዴ ለሁለት ቀን ያህል ተቋርጦ ይከርማል" ሲል ያማርራል።

የ 512 ሜጋ ባይት አቅም ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ከቴሌ ቢገዛም ቀርፋፋ እንደሆነ ያስረዳል። አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግ አቅሙ እንደማይፈቅድ የሚናገረው ተክለማርያም የውጭ ባለሀብቶች ድርጅቱን ቢገዙት አገልግሎቱ እንሚሻሻል ተስፋ ያደርጋል።

ትላልቅ የማሻሻያ እርምጃዎች

አሁን ያለውን የኢኮኖሚ ተግዳሮት ለማለፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ከማዞር ባሻገር ዋና ዋና የሚባሉ የኢኮኖሚ ማሻሻዮች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

አየለ ገላን በኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ላይ ምርምር የሚያደርግ ባለሙያ ነው። እንደ አቶ አየለ ከሆነ የኢትዮጵያን የምጣኔ ኃብት ችግሮች ከመነሻቸው መመልከት ተገቢ ነው።

"ወደ ውጪ የሚላኩ እንደ ቡና ሰሊጥና አበባ ያሉ የግብርና ምርቶችን በጥራትና በመጠን ለማሳደግ መስራት ያስፈልጋል" ይላል።

ለነመራ የበለጠ አሳሳቢ የሆነው ኢኮኖሚው በፌደራል መንግስቱ የተማከለ አስተዳደር ስር መሆን፣ ሙስናና ሰዎች የሚያገኙት ያልተገባ ጥቅም ናቸው።

"ፖለቲካውና ኢኮኖሚው በፌደራል መንግስቱ በከፍተኛ ደረጃ በማዕከል ተይዘዋል። በክልሎች ያልተማከለ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል።"

እንደባለሙያው ከሆነ ክልሎች እና የአካባቢ አስተዳደሮች እንደ ውሃ እና መብራት ያሉ አገልግሎታቸውን ለማስተዳደር ጠንካራ መሆን ይገባቸዋል። ሙስናን ለመዋጋትም ጠንካራ እርምጃ ያስፈልጋል።