ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ሦስተኛ ወገን አልነበረበትም ተባለ

የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በቅርቡ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዳልነበረበት አስታወቁ፡፡

ጽ/ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባለፉት 100ቀናት የተቀዳጇቸውን የውጭ ጉዳይ እና ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን በዘከረበት መግለጫ ላይ ፤ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት ለማቆም የተደረሰውን መግባባት ‹ትልቅ ድል› ሲል ገልጾታል፡፡ ስምምነቱ ‹‹ያለምንም ጣልቃ ገብነት እና ሽምግልና የተፈረመ›› ነው ሲልም አክሏል፡፡

ከስምምነቱ በፊት የተባበሩት አረብ ኤመሬትስን የመሰሉ ሀገራት በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም እንዲሰፍን ጥረት እያደረጉ ስለመሆናቸው መሰማቱ አይዘነጋም፡፡

በዛሬው ዕለት በወጣው የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ አንጋፋ ጋዜጣ ከሃሊጅ ታይምስ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ፣በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካካል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የልዑል ሼክ መሃመድ ቤን ዛይድ ‹ከፍተኛ ጥረት› ውጤት መሆኑ መናገራቸውን ብሎም ምስጋና ማቅረባቸውን አስነብቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጽ/ቤቱ ባለፉት 100 ቀናት ኢትዮጵያ የወሰደቻቸው ርምጃዎች የምስራቅ አፍሪቃ ቀጠና ጂኦፖለቲካል ሁናቴን ለማረጋጋት ፣ኢጋድን የመሰሉ ቀጠናዊ ተቋማትን ለማጠንከር የነበረውን ሚና ዘርዝሯል፡፡