"መኖር የምፈልገው ልጆቼን ለማየት ብቻ ነው"

አዲስ ዓለም ከትንሿ ልጁ ጋር Image copyright Addisalem Hadigu
አጭር የምስል መግለጫ የአዲስ ዓለም ትንሿ ልጁ ወታደር ናት

ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ አዲስዓለም ሀድጉ ለ16 ዓመታት ኤርትራ ውስጥ የሚገኙትን ባለቤቱንና ሁለት ሴት ልጆቹን አላያቸውም።

ከሁለት ዐሥርታት በላይ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ወደ ሰላም መመለሱና ጦርነቱንም ለማቆም የፈረሙት ስምምነት ተከትሎ የአዲስዓለም ተስፋ ታደሰ። ቤተሰቦቹን በዓይነ ሥጋ የማግኘት ተስፋው አንሰራራ።

በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመር የሚጠበቀው የአየር በረራ ብዙ ቤተሰቦች እንዲናፍቁት የኾነውም ለዚሁ ነው።

የኢትዮጵያና ኤርትራን የአብሮነት እርምጃ ምን ይፈትነዋል?

ለዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነት መመለሱ ጋር ተያይዞ ብዙዎች ናፍቆታቸውን በስልክ ለመወጣት ቢሞክሩም በድንበሩ ጦርነት ትዳሩ የፈረሰዉና ቤተሰቡ ለሁለት የተከፈለው አዲስዓለም ግን አሁንም በጉጉት እየጠበቀ ነዉ።

በሁለቱ አገራት ጦርነት ምክንያት ከመቶ ሺዎች በላይ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን አስከትሏል፤ ከዚህም በላይ በሕዝቦች መካከል መቃቃርን ፈጥሮ የጠላትነት ስሜት እንዲጎለብት አድርጓል።

አዲስ ዓለም የደረሰበትን ሁኔታ በአንደበቱ እንዲህ ይተርከዋል።

ወደ አሥመራ ለመጓዝ ማወቅ የሚገባዎ 6 ነጥቦች

ሁለት ወንድሞቼን በዚህ ጦርነት አጥቻለሁ። የጦርነቱ ጦስ ቤተሰቤንም አሳጥቶኛል። ከባለቤቴ ምፅላል ጋር የተጋባነው በ1972 ዓ.ም ነው። ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ልጅም አፍርተናል። በ1994 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ሁለት ሴት ልጆቼን ይዛ ከሄደች በኋላ ተያይተን አናውቅም። ኤርትራዊ በመሆንዋ ከምታስተምርበት ሥራ ስትባረር፤ ካገርም ሊያባርሯት ይችላሉ ብዬ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያዊ አግብታ እንደምትኖር ወረቀት አዘጋጅቼ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት ግን ኤርትራ ባካሄደችው ሕዝበ-ውሳኔ ላይ በኔ ተነሳሽነት ለነፃነት ድምፅ ሰጥታ ነበር። በወቅቱ እሷ ስጋት ቢኖርባትም ልጆቼ አባታቸው ከትግራይ መሆኑን እናታቸው ደግሞ ከኤርትራ መሆኗን እንዲያውቁ በማለት አደፋፍሬያት ድምፅ ሰጠች።

ይህ ሕዝበ-ውሳኔም ሥራዋን እንድታጣና ኤርትራም እንድትሄድ ምክንያት ሆነ። ትዳራችንም አከተመ።

የሞትኩ ያህል ነበር የመሰለኝ

ትናንትና የተፈጠረ በሚመስል ሁኔታ የሆነውን በዝርዝር አስታውሰለሁ።

ቀኑ ሮብ ነበር፤ ባለቤቴ አጎቷን ለመጠየቅ ሌላ ከተማ እንደምትሄድ ነገረችኝ። አጎቷም ቤት አልሄደች። ልጆቼን ይዛ ኤርትራ ገባች። ኤርትራ ለመሄድ አቅዳው የነበረ ቢሆንም ለኔ ግን ምንም ያለችኝ ነገር አልነበረም። ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ፤ በሕይወት መኖሬ ትርጉሙ ጠፋኝ። ኤርትራ ውስጥ ይህ ነው የምትለው ቤተሰብ ባይኖራትም የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ውስጥ ገባች።

የሁለቱም ሀገራት ድንበር በመቋረጡ ተከትያትም መሄድ አልቻልኩም፤ የሞትኩ ያህል ነው የተሰማኝ።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከመቶ ሺዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ደብዳቤ ምላሽ አልነበረውም

ባለቤቴ ሳትነግረኝ በድንገት መሄዷ ለቤተሰቦቼ አልተዋጠላቸውም። "አንድ ነገር ብታደርጋት ነው እንጂ እንዲህ ብን ብላ አትጠፋም ነበር" ይሉኝ ነበር። እኔ ግን ምንም እንዳልበደልኳት አውቃለሁ። በጣም የምንዋደድና የምንከባበር ባልና ሚስት ነበርን። ቤታችን ሳቅና ደስታ ተለይቶት አያውቅም ነበር።

ስትሄድ ጎረቤቶቼ ጋር የተወችልኝ ደብዳቤ ሲሆን "መለያየት ከሞት በላይ እንደሚከብድ አውቃለሁ፤ ሆኖም ልጆቼን ይዤ ሄጃለሁ። ወንዱ ልጃችንን አንተ ጋር ትቼዋለሁ። አጋጣሚውን ካገኘሁ ደብዳቤ እጽፍልኸለሁ፤ ለማንኛውም እራስህን ጠብቅ" የሚል ነው።

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ?

ለሳምንት ያህል ሐዘን ተቀምጫለሁ፤ ጎረቤቶቼም ሊያፅናኑኝ ቢሞክሩም ለኔ ሕይወት ያከተመች መስሎ ነበር የተሰማኝ። እንዳበደ ሰው በቁሜ የሞትኩ ያህል ይሰማኝ ነበር። የባለፉትን ዓመታት በቃላት ልገልጻቸው አልችልም። ሐዘኑን ለመርሳት ምርጫዬ የነበረው መጠጥ ብቻ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ኤርትራ ከመሄዳቸው በፊት፤ ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ይኖራቸዋል የሚል ሐሳብ አልነበረኝም። በፍፁም!

የትናንትናዋ እለት- በኢትዮ ኤርትራ ግጭት ቤተሰባቸው ለተለያየ?

ባለቤቴም ሆኑ ልጆቼ እድሉን አግኝተው ወደ ውጭ ሀገር ቢሄዱ መገናኘት እንደምንችል ተስፋ አደርግ ነበር።

በቀይ መስቀል በኩል በተከታታይ ደብዳቤ ብጽፍም ምላሽ አላገኘሁም። ተስፋ ስለቆረጥኩም የኋላ ኋላ መጻፍ አቆምኩ። ሁልጊዜም ግን ወደፊት አንድ ቀን ግን ባለቤቴን አግኝቻት ለምን ትታኝ እንደሄደች መጠየቅ እፈልግ ነበር።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በኤርትራ የሚገኘው ይህ መካነ-መቃብር የጦርነቱ አሰቃቂነት ማስታወሻ ነው።

ልጄ!

ሴቶች ልጆቼን በፌስቡክ ለማግኘት እየሞከርኩ በነበርኩበት ወቅት ትንሿ ሴት ልጄ ዳናይት በፌስቡክ መልእክት ላከችልኝ።

"በድምፅ ልናዋራህ አንችልም፤ ግን ሁልጊዜም ቢሆን እናስብኻለን" የሚል ነበር። እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። ናፍቆቴ ከቃላት በላይ ነበር።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከቴክኒክ ኮሌጅ ተመርቃ ሳዋ ወታደራዊ ካምፕ ስትገባ ግንኙነታችን ተቋረጠ። ወታደር በመሆኗ ስልክ ስለማይፈቀድ መገናኘታቸንም የመይታሰብ ሆነ።

ከዚህ በኋላ ሕይወት እንዴት ሸክሟ እንደከበደብኝ! ደግሞም ሁሉንም ልጆቼን ብወዳቸውም ለምን እንደሆነ አላውቅም ለትንሿ ልጄ ያለኝ ፍቅር ይለያል።

እንዴት ብዬ እንደምገልፃት አላውቅም። አስተዋይ፣ ከዕድሜዋ በላይ አሳቢ፣ የራሷ ያልሆነ ነገር የማትወድ ንፁህ ልጅ ናት። ልጆቼን ማግኘት የየዕለት ምኞቴ ነው። አንድ ቀን ተገናኝተን የዚህ ሁሉ ዓመታት የልብ ናፍቆታኝንና ያሳለፍነውን መጥፎ ታሪክ በለቅሶ እንዲወጣልን እመኛለሁ። የስልክ አድራሻቸውንም እየፈለግኩ ነው።

አሁን የ58 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ነኝ። ከዚህ በላይ የመኖር ፍላጎቱ የለኝም። ልጆቼንና ባለቤቴን ዳግመኛ የማገኝበትን ቀን ለማየት ብቻ ነው መኖር የምፈልገው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አዲስ ምዕራፍ

ሊገዳደሉ ከአንድ ጦር አውድማ የተገኙ ወንድማማቾች

አዲስዓለም አዲስተስፋ

ልጆቼን በህልሜ አያቸዋለሁ። ባለፈው ዕሁድ ኤርትራውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ሲቀበሉ ልጆቼንና ባለቤቴን ያየሁ ነው የመሰለኝ።

ቤተሰቤንና የድሮ ጓደኞቼን አግኝቼ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ወደ ኤርትራ መሄድ እፈልጋለሁ። ልጄም እናቱንና እህቶቹን እንዲያገኝ እፈልጋለሁ።

የልጆቼን እጆች መንካት፣ ፀጉራቸውን መዳበስና ጠረናቸውን ማሽተት ይናፍቀኛል። አሁን ትልቅ ሰውም ስለሆንኩ "አባዬ አለንልህ!" እንዲሉኝ እሻለሁ።

ይህቺ ቀን ከመጣች ለኔ ዳግም ውልደቴ ናት።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ