ትራምፕ አፍሪካን "ከክፋት ቅርቃር" ለማውጣት እንደሚሠሩ ቃል ገቡ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአህጉሪቱን ስምና ዝና ከፍ ዝቅ በማድረግ ዶናልድ ትራምፕን የሚያህል የለም።

የ72 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ትራምፕ ብራስልስ ለኔቶ ስብሰባ በተገኙበት ጊዜ ነው ስለ አፍሪካ የተናገሩት።

"አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች በማይረዱት የክፋት ቅርቃር ውስጥ ናት" ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህንኑ ለመቀየር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል። ስለ አህጉሪቱ ከአንደበታቸው መልካም አይወጣም የሚባሉት ትራምፕ አፍሪካን ዳግም ያነሱት በኔቶ ስብሰባ ማብቂያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

"ያሳዝናል! አፍሪካ ውስጥ አስቀያሚና ክፉ ሁኔታ ነው ያለው" ያሉት ትራምፕ የአሜሪካንን ወታደራዊ አቅም በማጎልበት ለዓለም ሰላም ማምጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን እንሻለን

ዶናልድ ትራምፕ በቅጡም አያውቁትም ስለሚባለው አህጉር አስተያየት ሊሰጡ የቻሉት ከስብሰባው ፍጻሜ በኋላ የቱኒዚያ ጋዜጠኛ አሜሪካ በሰሜን አፍሪካ አክራሪዎችን ድባቅ ለመምታት የምታደርገውን ጥረት አዳንቆ አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ ነው።

"አፍሪካ ውስጥ እየሆነ ስላለው ነገር እዚህ ክፍል ውስጥ አንዳችሁም የምታውቁት አይመስለኝም" ያሉት ትራምፕ እርሳቸው በየዕለቱ በሚቀርብላቸው የደኅንነት ሀተታ አህጉሪቱ የከፋ ሁኔታ ላይ እንዳለች እንደሚሳይ ጠቁመዋል።

"እኔ በደኅንነት ቢሮዬ በኩል የማያቸውን ነገሮች ብታዩ፣ አፍሪካ ውስጥ እየሆነ ያለው ክፉ ነገር በተረዳችሁ ነበር" ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለአህጉሪቱም ሆነ ለዓለም ሰላም ለማምጣት እያደረጉ ያሉትን ተናግረዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ወደድንም ጠላንም ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ላይ ከወጡ አንድ አመት ሞልቷቸዋል።

"በአፍሪካ ሰላም ማምጣት እንፈልጋለን፣ ዓለም ሰላም እንድትሆን እንፈልጋለን። ይህ ቀዳሚ ፍላጎቴ ነው። ይህን ለማሳካት ምድር አይታው የማታውቅ ወታደራዊ አቅም እየገነባን ነው" ብለዋል።

የትራምፕ ንግግርን ተከትሎ በትዊተር በርካታ ሰዎች አስተያየት የሰጡ ሲሆን ብዙዎቹ ምዕራቡ ዓለም አፍሪካን የሚያይበት የተንሸዋረረ አመለካከት የሚነቅፉ ናቸው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ትራምፕ አፍሪካ ውስጥ አዲስ ሀገር አገኙ!

ኤሊዛቤት ሜራብ የተባለች ኬንያዊት ጋዜጠኛ በትዊተር ገጿ "አፍሪካ አህጉር እንጂ አገር አይደለችም፤፤ በአፍሪካ 54 አገራት ይገኛሉ" ስትል ብስጭቷን ገልጻለች።