ኤርትራዊያን ሊያዩ የሚሿቸው አምስት ለውጦች

የውትድርና አገልግሎት

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም ወርዷል፤ የሁለቱ ሃገራት ፍቅርም እየጠነከረ መጥቷል። በጦርነት እና ሰላም እጦት ሲቆራቆዙ የከረሙት ሁለቱ ሃገራት ወደ ሰላም መድረክ በመጡበት በዚህ ጊዜ ኤርትራውያን በርካታ ጉዳዮች ተለውጠው ማየትን ይሻሉ።

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሃገራቸው ለሚታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው አለመስማማት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ኤርትራ ለ20 ዓመታት ያክል ባልተቋረጠ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ከርማለች፤ በተለይ ደግሞ ከድንበር ጦርነቱ በኋላ።

አሁን ላይ ግን ነገሮች እየተቀየሩ ይመስላሉ።

ሐምሌ 01/2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ታሪክ ሰሩ፤ ከ20 ዓመታት በኋላ አሥመራን በመጎብኘት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆንም ቻሉ።

ይህን ተከትሎም ሁለቱ ሃገራት በዲፕሎማሲውም ሆነ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሐምሌ 07/2010 ዓ.ም ሌላ ታሪክ፤ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ አዲስ አበባን ረገጡ።

ታዲያ እነዚህ ሁሉ በአጭር ጊዜ ይሆናሉ ተብለው ያልተጠበቁ ክስተቶች እውን እየሆኑ ባሉበት በዚህ ወቅት ኤርትራውያንን ሰቅዞ የያዘ አንድ ጉዳይ አለ፤ የሁለቱ ሃገራት ስምምነት ለኤርትራ ምን ትርፍ ይኖረዋል የሚል።

ተንታኞች በኤርትራ ቢያንስ አምስት ጉዳዮች ለውጥ ይሻሉ ይላሉ።

ሕገ-መንግሥት

ኤርትራ ነፃ ከወጣች ብዙም ጊዜ ሳይሆናት ነው የሕገ-መንግሥት ኮሚሽን በማቋቋም አዳዲስ ሕግጋትን ማርቀቅ የጀመረቸው።

ከሦስት ዓመታት በኋላም ሕገ-መንግሥቱ ለሃገሪቱ ብሔራዊ ጉባዔ ቀረበ፣ ከዓመት በኋላ የድንበር ጦርነቱ ተነሳ፤ ሕገ-መንግሥቱም በእንጥልጥል ቀረ።

በ1992 ዓ.ም የአልጀርሱ ስምምነት በሚፈርምበት ወቅት ሚኒስትሮች፣ ወታደራዊ አመራሮችና አንዳንድ ባለሥልጣናት ሕገ-መንግሥቱ መተግበር እንዲጀምር ጠየቁ።

ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት ጥያቄያቸውን ችላ አለው፤ አልፎም ይህን ጥያቄ ካነሱት መካከል 11 ሰዎች የገቡበት ጠፋ።

ኤርትራ እስከዛሬ ድረስ ሕገ-መንግሥት የላትም። ለ25 ዓመታት ኤርትራን የገዙት ኢሳያስ አፈወርቂም 'የሕግ ያለህ' የሚላቸው ሕግ ሳይኖራቸው ዘለቁ።

የኤርትራ ነገርም ምርጫ የለ፤ የሥልጣን ገደብ የለ፤ ሕገ-መንግሥት ሆነ።

ሕገ-መንግሥት ወይም በትግርኛው አጠራር 'ቅዋም' ለኤርትራ ሕዝብ ቀዳሚ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ ግን አልቀረም።

ሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊ ሆነ ማለት ፓርቲዎች በነፃ የሚንቀሳቀሱባት እና ነፃ ምርጫ የሚካሄድባት ሃገረ ኤርትራ እውን ትሆናልች ማለት ነውና።

ነፃ መገናኛ ብዙሃን

ወርሃ መስከረም 1993 ላይ የኤርትራ መንግሥት ሁሉም በግል የሚተዳደሩ ጋዜጦች የሕገ-መንግሥት ትግበራንና ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን በርዕስነት በማንሳታቸው እንዲዘጉ ወሰነ።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (ሲፒጄ) ቢያንስ 10 ጋዜጠኞች በወቅቱ ለእሥር እንደተዳረጉ መዘገቡ ይታወሳል።

ሰቲት፣ ዘመን፣ ቀስተ-ደበና፣ ፂጌና፣ መቃልህ እና አድማስ የተባሉ ጋዜጦች ድጋሚ ገበያ ላይ እንዳይታዩ ከተፈረደባቸው መካከል ነበሩ።

አሁን ላይ ኤርትራ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ሁሉም በመንግሥት የሚተዳደሩ ናቸው። የኤርትራ ቴሌቪዥን፣ ራድዮ ድምፂ ሓፋሽ እና በትግርኛ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛና ትግረ ቋንቋዎች የሚሰራጩ ጋዜጦች ገበያውን ያለተቀናቃኝ ተቆጣጥረውታል።

የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተመልክቶ ከሚወጡ ዘገባዎች አብዛኛዎቹ ኤርትራን በነፃ መገናኛ ብዙሃን ረገድ 'ጨቋኟ' ሃገር ሲሉ ይጠሯታል። 'የአፍሪቃ ሰሜን ኮሪያ' በሚል ቅፅል ስም በማጀብ።

ኤርትራውያን ይህ ስም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተፍቆ ማየት ይሻሉ።

የሃይማኖት ነፃነት

ኤርትራ ውስጥ እውቅና የተሰጣቸው አራት ሃይማኖቶች ብቻ ናቸው፤ የኦርቶዶክስ ክርስትና፣ የሱኒ እስልምና፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን እና የኤርትራ ኢንቫጄሊካል-ሉቴራን ቤተ-እምነት።

ከእነዚህ ውጭ ያሉት ሕገ-ወጥ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ አማኞች ለክስ የተጋለጡ ናቸው።

የሃይማኖት ነፃነት ላይ የሚሠራ አንድ የአሜሪካ ድርጅት ኤርትራ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለእሥር እንደተዳረጉ የዘገበው በቅርቡ ነበር።

የጄሆቫ ምስክሮችን ማደን የተጀረመው ኤርትራ ነፃ በወጣች ማግስት ሲሆን፤ ዋነኛ ምክንያት የነበረው ደግሞ ለኤርትራ ነፃነት ድምፃችንን አንሰጥም ማለታቸው ነበር።

በምድራዊ ፖለቲካ እና ብሔራዊ አገልግሎት ላይ ለመሳተፍ ካላቸው ቁጥብነት በመነሳት የእምነቱ ተከታዮች ዜግነት፣ የመኖሪያ መታወቂያ ካርድ እና የሥራ ፈቃድ አይሰጣቸውም።

ይህም ጉዳይ ሌላው ኤርትራዊያን ተቀይሮ ሊያዩት የሚሹት መብት ነው።

የብሔራዊ አገልግሎት ፍፃሜ

ብሔራዊ አገልግሎት ኤርትራ ውስጥ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከ1987 ጀምሮ ነው።

መባቻው ላይ ሁሉም ዜጎች ለ18 ወራት ብሔራዊ አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ታዘዘ፤ የ6 ወራት ወታደራዊ ሥልጠናን ጨምሮ።

ከ1994 ጀምሮ ግን የአገልግሎት ጊዜው ገደብ አልባ እንዲሆን ተደረገ።

ወጣት ኤርትራዊያን 11ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ወደሳዋ የማቅናት ግዴታ አለባቸው። እዚያም 12ኛ ይጨርሱና ወታደራዊ ሥልጠናውን ይቀላቀላሉ፤ መቼ እንደሚጨርሱ ግን ይፋ የሆነ ቀነ-ገደብ አልተቀመጠላቸውም፤ አንዳንዶችም ለዓመታት ያገለግላሉ።

በወታደራዊ ሕግጋት ሥር የሚቆዩት እኚህ ወጣቶች እንቅስቃሴያቸውም የተገደበ ነው።

ብሔራዊ አገልግሎት አንድ ሰሞን ለኤርትራዊያን የኩራት ምንጭ ነበር፤ አሁን ግን በርካታ ወጣቶች ሃገሪቱን ጥለው ይሸሹ ዘንድ ምክንያት ሆኗል።

የፖለቲካ እሥረኞች መፈታት

መቀመጫቸውን አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ያደረጉ ኤርትራዊያን እንደሚስማሙት ኤርትራ ውስጥ ለውጥ መታየት የሚጀምረው የፖለቲካ እሥረኞች ሲፈቱ እንደሆነ ነው።

የዚሁ ጉዳይ አንደምታ እስከ ብሔራዊ የጋራ መግባባት ድረስ ሊያደርስ እንደሚችል በርካቶች ያምናሉ።

ጂ-15 ተብለው ስለሚጠሩት የፖለቲካ እሥረኞች ብዙ የተባለ ሲሆን ስማቸው ያልገነነ ሺዎች አሁንም ከፍርግርጉ ጀርባ ይገኛሉ።

እሥር ቤቶቹም ደረጃቸው እጅጉን የወረደ ተብለው ሲብጥለጠሉ ይሰማል።

እሥረኞችን መፍታት ለኤርትራ ለውጥ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደውም ለዚህ ነው።