የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሰራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር Image copyright Getty Images

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሰራተኞች ከአሰሪዎች ጋር ባለ ችግር፣ ባልተመቻቸ የሥራ ቦታና በሥራ ጫና ችግር ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ ላይ መሆናቸውን ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የቋሙ ሰራተኞች ለቢቢሲ ገልፁ።

ሠራተኞቹ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት መስሪያ ቤታቸውን ለቀው እንዳይወጡ በፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ኩባንያው የቻይና ዜግነት ያላቸው የባቡር አሽከርካሪዎች ባቡሮቹን እንዲያንቀሳቅሱ ጠርተዋቸዋል።

በሃገሪቱ የተከሰቱት ቀውሶችና አዲስ አበባ

ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚወስዱ አውራ ጎዳናዎች

"በወር ከ330 ሰዓት በላይ ነው የምሰራው። የሚከፈለኝ ግን ከ175 እስከ 180 ሰዓት የሚሆነው ብቻ ነው" ነው የሚሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የባቡር አሽከርካሪ፤ ረዥም ሰዓታት ካለክፍያ መስራት ብቻ ሳይሆን ያልተመቻቸ የሥራ ሁኔታም ሌላ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ።

ከባቡር አሽከርካሪዎቹ (ትሬይን ማስተር) መካከል አንዱ እንደሚለው የሰራተኞቹ ጥያቄ ባቡሩ ሥራ ከጀመረበት መስከረም 8/2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲንከባበል የመጣ ነው።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አሰፋም ይህ ጥያቄ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ጉዳዩ ስድስት ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ቦርድ መታየቱንና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ብቻውንም መመለስ አይችልም በመባሉ ወደ ሌላ ሂደት መሸጋገሩን ተናግረዋል።

"ለአንድ ዓመት ሙሉ በበዓላትም ቀን ጨምር እንሰራ ነበር፤ ምንም እረፍት የለንም። ለምሳሌ በመጀመሪያ ቀን አንድ ሰው በማታ ፈረቃ 7̄ ሰዓት ከ 30 ገብቶ ሌሊት 6 ሰዓት ላይ ይጨርሳል፤ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ማታ 12 ሰዓት ድረስ ይሰራል" ሲል አንዱ አሽከርካሪ የነበረውን የሥራ ሁኔታ ይናገራል።

በእነዚህ ሁለት ቀናት ታዲያ ማደሪያቸው ባቡሮቹ በሚነሱባቸው አያት ወይም ቃሊቲ ባሉ የማረፊያ ክፍሎች ውስጥ የማደረግ ግዴታ እንዳለባቸው ነው ጨምሮ የተናገረው።

"ከማደሪያ ውጪ ወደየትም እንድንሄድ አይፈቀድም፣ ወደየትም መሄድ አይቻልም፣ ትራንስፖርትም የለም፣ አይፈቀድምም ይህን የተላለፈ ቅጣት ይጣልበታል። በሦስተኛው ቀን በማለዳው ፈረቃ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 4 ሰዓት ከሰራን በኋላ ነው መውጣት የሚፈቀድልን" ብሏል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ አየር መንገዶች በሽርክና ሊሰሩ ነው

ዶላር በጥቁር ገበያ ለምን ቀነሰ?

በአንድ ክፍል ውስጥ ስምንት ሆነው እንደሚያድሩ የሚገልጸው ሌላኛው የባቡር አሽከርካሪ አኗኗራቸው ጤናቸው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም አመልክቷል።

በዚህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት ምንም አይነት የተጨማሪ ሰዓት፤ የማታ ፈረቃ ክፍያም ሆነ የትራንስፖርት ጥቅማ ጥቅሞች ክፍያ ሳይፈጸምላቸው እንደሰሩና፤ ለዚህ ሥራቸውም በወር የሚያገኙት ደሞዝ በጣም አነስተኛ እንደሆነ ሰራተኞቹ ተናግረዋል።

እናም የሥራ ሁኔታቸው እንዲስተካከልና የማግኘት የሚገባቸው ጥቅማ ጥቅም እንዲከበር እንዲሁም የደሞዝ ጭማሪ እንዲደርግላቸው በመጠየቅ ሥራ እንዳቆሙ ተናግረዋል።

"ይህንን ጥያቄም በተደጋጋሚ ለአስተዳደሩ፣ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርም ሆነ ለባቡር ኮርፖሬሸን ብናቀብርም ምንም አይነት ምላሽ አላገኘንም። ማንም መጥቶ ያናገረን የለም አሁን ግን ሥራው ሲቆም መጥተዋል፣ ሊያነጋግሩንም ፍላጎት አሳይተዋል" ሲሉ ሰራተኞቹ ተናግረዋል።

ቻይናዊያኑ የባቡር አሽከርካሪዎች ከሁለት ዓመታት በፊት ቦታቸውን ለኢትዮጵያውያን አስረክበው መውጣታቸው የሚታወስ ነው። ባቡር አሽከርካሪዎቹ እንደሚሉት ከአንድ ዓመት በፊት ለስልጠና ቻይና ቲያንጂን ሳሉ ይህንኑ ጥያቄያቸውን ማንሳታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን የሥራ ማቆም አድማውን በተመለከተ "በቅርቡ ከተቋቋመው የሰራተኛ ማህበር ጋር ለረጅም ጊዜ ድርድር ከተደረገ በኋላ ስምምነት ተደርሷል። በእኔ እይታ የብዙ ጊዜ ጥያቄያቸው የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ ዛሬ አድማ ለመምታት አይዳርግም" ብለዋል።

ማደሪያዎቹንም በተመለከተ ሲናገሩም የተዘጋጁት ሰራተኞቹ አረፍ እንዲሉበት እንጂ እንደመኖሪያ እንዲቆጠሩ እንዳልሆነ አመልክተው፤ "ሌሊት ለሚገባ ሰራተኛ ለራሱ ሲባል ማታ አርፎ ጠዋት ሥራ የሚቀጥልበትን ፣ ቤት መሄድ የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ አርፎ ለቀጣይ ሥራ ሙሉ ኃይል የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት የተዘጋጁ ናቸው" ብለዋል።

የባቡር አሽከርካሪዎቹ ከዚህ ቀደም አራት ባልደረቦቻቸው ለምን ጥያቄ አነሳችሁ በሚል ከሥራ መባረራቸውንም ይገልፃሉ።

ባለሙያዎቹ እንዳሉት አድማ በመምታታቸው በከተማዋ በሁሉም አቅጣጫዎች የባቡር ጉዞ አገልግሎት ተቋርጧል።

ተያያዥ ርዕሶች