የኤርትራ መንግሥት የሐይማኖት እሥረኞችን ፈታ

ኤርትራውያን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የኤርትራ መንግሥት በሃይማኖት ምክንያት የታሠሩ 35 እሥረኞች ትላንት ምሽት አካባቢ መፍታቱ ተሰምቷል። እሥረኞቹ የተፈቱት ማይስርዋ ተብሎ ከሚታወቀው ማረሚያ ቤት ነው።

ከተፈቱት 35 ግለሰቦች መካከል 14 ሴቶች ሲገኙ የጴንጤቆስጤ ቤተክርስትያን አባላት መሆናቸው ታውቋል።

ትላንት ከሰዓት ገደማ 30ዎቹ እንደተለቀቁ ከተሰማ በኋላ ማምሻው ላይ ደግሞ የተቀሩቱ 5 ግለሰቦች ከእሥር ተፈተዋል።

ከተፈቱት መካከል ታናሽ ወንድሙ የሚገኝበት ዳንኤል «ወንድሜ መፈታቱ እጅግ አስደስቶኛል» ሲል ስሜቱን ለቢቢሲ አጋርቷል።

እንደ ዳንኤል ገለፃ ታናሽ ወንድሙ በሐይማኖቱ ምክንያት ለ1 ዓመት ከ8 ወራት በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ለእሥር ተዳርጓል፤ ቤተሰቦቹም ታሣሪ ልጃቸውን ፍለጋ ብዙ ተንገላተዋል።

ከ35 ግለሰቦቹ አንዱ ለ8 ዓመታት ያክል እሥር ቤት እንደቆየ የተቀሩቱ ደግሞ ከ1 እስከ 4 ዓመት ድረስ እንደታሰሩ ሰምተናል።

ማይስርዋ ከከረሙት እሥረኞች ከሶስት ሳምንታት በፊት እንደሚፈቱ ተነግሯቸው ቅፅ እንደሞሉ ነገር ግን ወዲያው እንዳልተፈቱ ታውቋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእሥረኞቹ መፈታት ኤርትራና ኢትዮጵያ ከደረሱት የሰላም ስምምነት ጋር የሚገናኝ አይደለም።

ምንጮቹ እንደሚገልፁት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አስመራን በጎበኙበት ወቅት የታሠሩ ግለሰቦች አሉ።

የኤርትራ መንግሥት በ1994 ላይ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስትያናትን ሙሉ በሙሉ መዝጋቱ ይታወሳል።

የሰብዓዊ መብት ቡድኖች የኤርትራ መንግሥት በሺህ የሚቆጠሩ ግለሰቦችን በሐይማኖት እና ፖለቲካ ምክንያት አስሯል ሲሉ ይወቅሳሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኤርትራ መንግሥትን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።