ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ንግድ ትስስር ማን ይጠቀማል?

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስና አቶ ዳፍላ
የምስሉ መግለጫ,

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ግራ) እና አቶ ክብሮም ዳፍላ (ቀኝ)

የኢትዮጵያና የኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ከምንም በላይ በብዙ መንገድ ተሳስረው ሳለ ለዓመታት ለተለያዩት የሁለቱ አገራት ህዝቦች መገናኘት ትልቅ ነገር መሆኑ አያጠራጥርም።

የሰላሙ ወደ ንግድ ግንኙነት መሸጋገር ደግሞ አገራቱን ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይጠበቃል። ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም ትልቅ እፎይታ ሲሆን ኤርትራንም አትራፊ ያደርጋታል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ አየር መንገዶች በጋራ መስራትም ሌላው የንግድ ትስስር መስመር ነው። ከእነዚህና ከሌሎችም የንግድ ትስስሮች አገራቱ ሲጠቀሙ ህዝቡም ተጠቃሚ እንደሚሆን አይጠረጠርም።

የሰላም እርምጃው ለሁለቱ አገራት ህዝቦች መገናኘትና አብሮ መኖር ትልቅ ነገር ቢሆንም ከንግድ ግንኙነቱ ኤርትራም እንደ አገር እንደማታተርፍ ህዝቡም እንደማይጠቀም የሚናገሩ አሉ።

የኤርትራ አገር ውስጥ ገቢ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊ፣ ከዚያም ለሶስት ዓመታት የኤርትራ አየር መንገድ ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን ለዓመታት ያገለገሉት አቶ ክብሮም ዳፍላ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ናቸው።

ስለ ኤርትራ መንግሥት ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃ በጥቅሉ ስለ አገሪቱ ኢኮኖሚ በቅርበት የሚያውቁት አቶ ክብሮም "የሁለቱን ህዝቦች ልብ የሚያሳርፍ በመሆኑ የግንኙነቱ መጀመር ትልቅ ነገር ነው" ቢሉም በተለይም ከንግድ ግንኙነቱ ኤርትራና ኤርትራዊያን አይጠቀሙም ሲሉ ያስረግጣሉ።

ኢትዮጵያ ሰፊ የንግድ ስርአት ያላት አገር በመሆኗ ከኤርትራ ጋር የተለያዩ የንግድ ስምምነቶችን ስታደርግ ኢትዯጵያዊያን ኢንቨስተሮች ኩባንያዎች ታሳቢ ተደርገው ሲሆን በተቃራኒው በኤርትራ በኩል ግን የዚህ አይነት መዋቅር አለመኖር በቀዳሚነት የሚያስቀምጡት ነጥብ ነው።

"በኢትዯጵያ በኩል ነገሮች ክፍት ናቸው። በኤርትራ በኩል ደግሞ ነገሮች ዝግ የተደረጉት እንዲሁ ሳይሆን በህግና በስርዓት ነው። ይህ የወጪ ንግድ ላይም ይሁን ገቢ ላይ ኢትዮጵያዊያን ያለ ውድድር መሳተፍ የሚችሉበት እድል ይፈጠራል። ኤርትራዊ ምንም ውስጥ አይገባም ማለት ነው" የሚሉት አቶ ክብሮም ዘላቂ መሆኑ ቢያጠራጥርም አጋጣሚው ለኢትዮጵያ ሎተሪ ነው ይላሉ።

የንግድ ሽርክናውን የሚሸከም ስርአት ኤርትራ ውስጥ እንደሌለና ይህም 20 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይናገራሉ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ህዝብ ምንም ስለማይጠቀም ለተጠቃሚነቱ የተዘጉ በሮች ሁሉ እንዲከፈቱ ህዝቡ መጠየቅ እንዳለበት ያሳስባሉ።

ከኤርትራ ጋር በሚደረገው የምጣኔ ሃብት ትስስር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ይጠቀማሉ ቢሉም በኤርትራ በኩል ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት እስካልተዘረጋ ድረስ የኢትዮጵያ ጥቅምም እንደታሰበው ሊሄድ እንደማይችል አቶ ክብሮም ያስረዳሉ።

እንደ እሳቸው ገለፃ አሁን ኤርትራ ውስጥ ባለው እውነታ የንግድ ትስስሩ በኢትዮጵያ ብቻ ወደ ፊት ሊራመድ ስለማይችል የመገታት አደጋ አለበት።

የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረው የንግድ ትስስር እንደ ባንክ ባሉ ተቋማት እና የፋይናንስ ሥርዓት ካልታገዘ በቀር ለሳቸው ነገሩ ቴአትር እንጂ ሌላ አይሆንም።

በጥቅሉ ለሳቸው ይህ ነው የሚባል የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት ስርዓት ከሌሎው የኤርትራ መንግስት ጋር የሚደረግ ንግድ ለኤርትራዊያን ምን ጠብ የሚያደርገው ነገር አይኖረውም። በኢትዮጵያ ብቻም ወደ ፊት ሊራመድ አይችልም።

በተስፋ ላይ ተስፋ

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ጅቡቲ ወደብ ላይ ባለው ጫና እቃዎች ከስድት ወር በላይ ወደቡ ላይ እየተቀመጡ በመሆናቸው ከመቸገሯም አልፎ በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር እየከፈለች ላለችው ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች መጠቀም ትልቅ ነገር እንደሆነ ይገልፃሉ።

ከኤርትራ አየር መንገድ ጋር በሽርክና ለመስራት የተስማማው የኢትዮጵያ አየር መንገድም በትልቁ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያምናሉ።

የኤርትራን አየር ክልል ማቋረጥ ባለመቻል ሲደረጉ የነበሩ ረዥም በረራዎችን አሁን ማሳጠር በመቻሉም የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተጠቃሚ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ።

በተለይም ለምፅዋ ወደብ ቅርብ የሆኑት ትግራይና አማራ ክልሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ያመለክታሉ።

ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ የኤርትራ ወደቦችን ኢትዮጵያ ስትጠቀም የስራ እድሎች እንደሚፈጠሩና የኤርትራ ህዝቦች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋ አላቸው።

ተስፋቸው ግን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ መጥተው ከተናገሯቸው ነገሮች በመነሳት በቀጣይም አገሪቷ ህገመንግስቷን በማፅደቅ ህዝቡም መሪውን ይመርጣል በሚል ተስፋ ላይ የተመሰረተ ነው።

ነገሮች ካልተቀየሩ ትልቁ ችግር ለኤርትራ እንጂ ለኢትዮጵያ እንደማይሆን ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ ከጅቡቲ፣ ከሶማሌላንድና ከሱዳን ጋር ራስዋ የምትቆጣጠረው ወደብ ለማግኘት እየተነጋገረች መሆኗን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ።

ኤርትራዊያን ወጣቶች ለጦርነት የሚዘጋጁ ሳይሆኑ አምራች የሚሆኑበት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኤርትራ ዲያስፖራ በአገር ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርግበት ሥርዓት ካልተዘረጋ ነገሩ ሁሉ ትርጉም እንደማይኖረው አገሪቱንም ወደ ቀደመ ቀውስ ሊመልሳት እንደሚችል ያመለክታሉ።

በኤርትራ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ህዝቡ ጥረት ሊያደርግ እንሚገባ ያምናሉ። በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የተጀመረው ግንኙነትም አዎንታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረውም ተስፋ ያደርጋሉ።