ዶናልድ ትራምፕ ፑቲን አሜሪካን እንዲጎበኙ ጋበዟቸው

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በሩሲያ በኩል እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን በፀደይ ወቅት አሜሪካን እንዲጎበኙ እንደጋበዟቸውን የዋይት ሀውስ አፈ ቀላጤ አስታወቁ።

ሳራ ሳንደርስ ጉብኝቱን በተመለከተ ንግግሮች መጀመራቸውንም ገልፀው ሁለቱ መሪዎች ከጥቂት ቀናት በፊት በፊንላንድ ሄልሲንኪ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን የተወያዩባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ ሳያደርጉ ቀርተዋል።

ሁለቱ መሪዎች መገናኘታቸውን ተከትሎ ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ነገር ውዝግብ አስነስቶ የነበረ ቢሆንም ሰውየው ግን በመጨረሻ ውይይቱ በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከዚያም በቀጣይ እንደገና እንደሚገኛኙ ቢያመለክቱም እስካሁን በሩሲያ በኩል ትራምፕና ፑቲን ዳግም ሊገናኙ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።

የፑቲን 'አሜሪካን ጎብኙ' ግብዣን በተመለከተ የተለያዩ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በተለያየ መልኩ ስሜታቸውን እየገለፁ ነው።

የቀጥታ ስርጭት ቃለ ምልልስ ላይ ሳሉ ዜናውን የሰሙት የአሜሪካው ብሄራዊ ደህንነት ፎረም ዳይሬክተር ዳን ኮትስ "ነገሩ ልዩ ይሆናል"ሲሉ በመሳቅ ነበር መልስ የሰጡት።

• ትራምፕ ከፑቲን ጋር በተያያዘ ወቀሳ እየዘነበባቸው ነው

ጨምረውም አስተርጓሚዎቻቸው ብቻ በተገኙበት የትራምፕና የፑቲን ውይይት ምን እንደተወራ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ገልፀዋል።

በአሜሪካ ምክር ቤት የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ የሆኑት ቻክ ሹመር ሁለት ሰዓታት በወሰደው የትራምፕና የፑቲን ውይይት ምን እንደተወራ ትራምፕ እንዲናገሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።

"ምን እንደተነጋገሩ እስካላወቅን ድረስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ፣ ሩሲያም ይሁን ሌላ ቦታ እንደገና ከፑቲን ጋር ለብቻቸው ዳግም እንዲወያዩ መፈቀድ የለበትም" ብለዋል።