'ሃሰተኛ ዜና '፡ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ስጋት

'ፌክ ኒውስ'፡ የኢትዮጵያ ስጋት

ሁሉም ጋዜጠኛ በሆነበትና ተጠያቂነት በሌለበት በማህበራዊ ድር አምባ ዘመን 'ፌክ ኒውስ' ወይም 'ሃሰተኛ ዜና' በከፍተኛ መጠን እየተሰራጨ ነው።

በተለይም የሃገራት የሚዲያ ሕጎች በዜጎች ላይ ተግባራዊም ስለማይደረጉባቸው ሃሰተኛ ዜናዎችን ለግልም ይሁን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ማስፋፋት የተለመደ ሆኗል።

'ሃሰተኛ ዜና' ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እየተፍጨረጨሩ ላሉም ሆነ 'ዴሞክራሲን ለእኛ ተዉት' ላሉ ሃገራት አደጋ እየጋረጠ ያለ ጉዳይ ሆኗል።

ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አፍ ጠፍቶ የማያውቀው ይህ ቃል ፈረንጆቹ የ2017 አወዛጋቢው ቃል ሲሉ መርጠውታል።

ወደ ሃገራችን ስንመጣም ሃሳዊ ዜናዎች ለበይነ መረባዊ ጥቃት (ሳይበር አታክ) ከመዳረግ አልፈው በየሥፋራው እየተስተዋሉ ላሉ ማንነትን መሠረት ላደረጉ ግጭቶች መንስኤ እስከመሆን ደርሰዋል።

የፋይናንስና ኦዲቲንግ ባለሙያው አቶ ታምሩ ሁሊሶ በፌስቡክ ገፃቸው የሃሰተኛ ዜናዎችን በመንቀፍ ይታወቃሉ።

«ለሃሰተኛ ዜና አሰራጭ ግለሰቦች የአሁኑን የመሰለ የተመቻቸ ጊዜ እና ሁኔታ የለም፤ በተለይ ደግሞ በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ላይ» ይላሉ።

አቶ ታምሩ 'የሰጠ ጊዜ' ብለው የሚያስቀምጡት ወቅቱ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እዚህም እዚያም መነሳታቸውን ዋቢ በማድረግ ነው።

«ሰዉ አሁን ስጋት ላይ ነው ያለው፤ በእዚህ ስጋት ላይ እዚህ ቦታ እንዲህ ዓይነት ነገር ተፈጥሯል የሚል ሃሰተኛ ዜና ሲጨመርበት ከማመን ወደኋላ አይልም።»

እውነታ ጣል የተደረገበት ልብ-ወለድ

ሃሰተኛ ዜና ሰው ጆሮ እውነት ያለው ዜና መስሎ ይደርስ ዘንድ መጀመሪያ የተፈጠረ ነገር አለ ማለት ነው በማለት የማሕበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚው አቶ ተስፋዬ ሰሙንጉሥ ይናገራሉ።

በፌስቡክ ገፃቸው እውቀትን በማካፈል የሚታወቁት አቶ ተስፋዬ «ሃሰተኛ ዜና ከመሬት አይነሳም» ባይ ናቸው።

«ለምሳሌ. . .» ይላሉ አቶ ተስፋዬ «ለምሳሌ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ አንድ ሃሰተኛ ዜና ቢሰራጭ ተቀባይነት የማግኘቱ ነገር ሰፋ ያለ ነው። ብጥብጥ ያለበት ቦታ እንዲህ ዓይነት ነገር ተፈጥሯል በማለት ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት ያስተላልፋሉ።»

በእንግሊኛ አጠራሩ 'የሎ ጆርናሊዝም' በመባል የሚታወቀውን ሃሰተኛ ዜና የማሰራጨት ዘዴ አቶ ተስፋዬ «እውነታ ጣል የተደረገበት ልብ-ወለድ ሲሉ ይጠሩታል።

«ሰዎች ሃሰተኛ ዜናዎችን የሚያሰራጩት ለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ሊሆን ይችላል። በጎም ይሁን አሉታዊ ዓላማ ያዘለም ሆኖ ብናገኘው አይገርምም። ሰዎች ሃሰተኛ ዜና የሚያሰራጩት ማስታወቂያ ለመሥራት ሊሆን ይችላል፤ በጎ ሃሳብ ለማስተላለፍ አልያም ፕሮፓጋንዳቸውን ለማስፋፋትም ይሆናል።»

ከደመናው በላይ ያለ አደጋ

አቶ ተስፋዬም ሆነ አቶ ታምሩ የሚስማሙት ሃሰተኛ ዜናዎች ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ እንዳላቸው ነው፤ በተለይ ደግሞ አሁን ባለው የሃገሪቱ ሁኔታ።

«ጠንካራ ወገብ ያላቸው ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በሌሉበት፣ ሁኔታዎች ባልተረጋጉበት፣ ያኮረፉ ኃይሎች ባሉበት፣ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በሚታዩበት፣ ሰዎች ፍርሃት ተጭኗቸው እያየን ሃሰተኛ ዜና ማሰራጨት አደጋው ከፍ ያለ ነው» ሲሉ አቶ ታምሩ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

«ማዕከላዊ አፍሪካ በተከሰተ ግጭት ላይ የተነሳን ዘግናኝ ግድያ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ተለጥፎ የሚያምን ሰው ካለ ይህ የሚነግረን እንዲህ ዓይነት ድርጊት እኛ ሃገር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ያለበት ማሕረሰብ አለ ማለት ነው» ሲሉ ያክላሉ።

አቶ ተስፋዬ አደጋውን በማሕበራዊ፣ ሐይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ አንደምታው ከፋፍለው ያዩታል «ፖለቲካዊ አደጋው አንድን ሃገር ሙሉ በሙሉ እስከማውደም የሚደርስ ተፅዕኖ አለው» ሲሉ ያስረዳሉ።

«መሰል ዜናዎችን ለበጎ ዒላማ የሚጠቀሙባቸው ሰዎች ያሉትን ያህል በጎ ላልሆነ ዓላማ ጥቅም ላይ ሲውል የሚያመጣው አደጋ እጅጉን አስጊ ነው።»

ማንን እንመን. . .?

ታድያ ሃሰተኛ ዜናዎች በሚያሳምን መልኩ የሚመጡ ከሆነ ማንን እንመን? እንዴትስ ነው እውነታውን ከሃሰተኛው የምንለየው?

ለአቶ ታምሩ በተለይ ማሕበራዊ ድር አምባዎች ላይ የሚሰራጩ ዜናዎችን ለይቶ «ይህ ሃሰት ነው ይህ እውነተኛ ነው» ለማለት የሰዎች የማገናዘብ እና የትምህርት ደረጃ ወሳኝ ነው።

«ተረጋግቶ ማገናዘብ እንጂ እያንዳንዱ ሰው ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ የዜናውን እውነተኛነት ያራጋግጥ ማለት ከባድ ነው።»

አቶ ተስፋዬም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፤ «የዜናው ምንጭ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ እጅጉኑ ያሻል» ይላሉ።

«ለምሳሌ እናንተ አንድ ዜና ስትሰሩ የድርጅታችሁን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ተከትላችሁ፣ መረጃ፣ ማስረጃ ሰብስባችሁ እማኝ አናግራችሁ ነው። ሌላውም ተዓማኒነት ያለው ተቋም የሚያደርገው ይህንኑ ነው። ታዳሚያን ይህንን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ ያስፈልጋል።»

«ዜናውን አይተን ወዲያውኑ ፍርድ ከምንሰጥ ይልቅ ማጣራት መልመድ ብንችል በጎ ነው፤ ዜናው ካጠራጠረን ቢያንስ ጉግል ብናደርግ የተሻለ ነው» ሲሉ አቶ ተስፋዬ ይመክራሉ።

«ሃሰተኛ ዜናዎችን የሚያመጡትን አደጋ ለመዋጋት የማሕበረሰቡ ንቃተ ኅሊና ወሳኝ ነው፤ የትኛው ተቋም ነው ይህን ዜና ያሰራጨው? የትኛው ግለሰብ? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊነቱ ላቅ ያለ ነው። ጊዜን እና ሁኔታን ከግምት ውስጥ ማስገባትም ያሻል» ይላሉ አቶ ተስፋየ።

«መንግሥት ደግሞ. . .» ይላሉ አቶ ታምሩ «መንግሥት ደግሞ ሕብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ ጠዋት ማታ ሳይል ሊሠራ ይገባል፤ ዋናው ነገር እሱ ነው። ነገ መጥፎ ነገር ይከሰታል የሚለውን ጭንቀት ከሕብረተረሰቡ ውስጥ መንቀል አለበት» ባይ ናቸው።

ከሃሰተኛ ዜና እንጠበቅ!!!

ሃሰተኛ የሆነ ዜና አጋርተው ወይም ተጋርተው ያውቃሉ? እዚህ ቦታ ቦንብ ፈነዳ. . . እከሌ/እከሊት እኮ ሞተ/ሞተች. . .ብቻ ትኩስ ያሉትን ዜና ለወዳጅ ዘመድዎ አጋርተው/ተጋርተው ያውቁ ይሆን?

ቆም ብለው ይህ ነገር እውነት ይሆን ወይስ የተፈበረከ ነው ብለው ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? ባለሙያዎች ይህን እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

ዜናውን ከማጋራትዎ በፊት ታማኝ ከሚሉት ምንጭ መምጣት አለመምጣቱን ያረጋግጡ፤ ጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን፣ ራድዮ ወይም የበይነ መረብ ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ ብቻ ማረጋገጥ የመጀመሪያ ሥራዎ መሆኑን አይዘንጉ።

ዜናው ታማኝ ከሚሉት አንድ ምንጭ መጥቶም ሊሆን ይችላል፤ ሌሎችስ ስለዚህ ዜና ምን አሉ? ብለው ራስዎን ይጠይቁ።

ተንቀሳቃሽ ምስል ሊሆን ይችላል ወይም ፎቶግራፍ ምን ያህል እውነት ያዘለ ነው? ብለው መመርመርዎንም አይዘንጉ። ሃሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦች ተመሳሳይ ይዘት እና ቅርፅ ያላቸው ፎቶዎችም ይሁኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከማዛመት ወደኋላ አይሉምና።

በተለይ ፌስቡክ እንዲሁም ዩትዩብ የተሰኘው የተንቀሳቃሽ ምስል መጋሪያ መድረክ ላይ ከማስታወቂያ ገንዘብ ለማግኘት ብለው ሃሰተኛ ዜና የሚያሰራጩ የበረከቱበት ዘመን ነው።