በወለጋ የአራት ቀን ሬሳን ከሞት አስነሳለሁ ያለው ነብይ ነኝ ባይ የሟች ቤተሰብን እንዴት ሊያሳምን ቻለ?

Image copyright Screen Capture/Facebook
አጭር የምስል መግለጫ እራሱን ነብይ ሲል የሚጠራው ግለሰብ ሟችን ለማስነሳት ጥረት በማድረግ ላይ

ባሳለፍነው ዓርብ በምሥራቅ ወለጋ የአራት ቀን ሬሳ አስነሳለሁ ብሎ መቃብር ያስቆፈረው 'ነብይ' ነኝ ባይ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

ይህ ግለሰብ ሙሉ ስሙ ጌታያውቃል አየለ ይባላል። የሟች ቤተሰቦች ለቅሶ ተቀምጠው ሳለ ነበር ቤታቸው ከተፍ ያለው። ለለቀስተኛው የመጽሐፍ ቅዱሱን አልአዛር ታሪክ በመንገር ሟች በላይን እንደሚያስነሳ በጽኑ ያሳመናቸውም ከዚያው ነበር።

የሟች ቤተሰቦችም በሞት ያጡትን በላይን ከሞት እንደሚያስነሳላቸው እምነት የጣሉበት ወዲያውኑ ነበር። እራሱን 'ነብይ' ብሎ ከሚጠራው ግለሰብ ጋር በመሆንም ወደ መቃብር ሥፍራው ወረዱ።

የሟች ግብዓተ መሬት ወደተፈጸመበት የሙሉ ወንጌል መካነ መቃብር ሥፍራ እንደደረሱ ጌታያውቃል መቃብሩን ማስቆፈር ጀመረ። የሬሳ ሳጥኑን ከከፈተ በኋላ በተደጋጋሚ ''በላይ ተነስ!'' እያለ ጮኸ። በመጨረሻም መልስ ያጣው ጌታመሳይ ''ምንም ማድረግ አይቻልም'' ብሎ ከመቃብሩ ጉድጓድ ወጣ። ከዚህ በኋላ ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው።

በምሥራቅ ወለጋ የአራት ቀን ሬሳ አስነሳለሁ ብሎ መቃብር ያስቆፈረው 'ነብይ' በቁጥጥር ሥር ዋለ

ሰባኪው አውሮፕላን ግዙልኝ አለ

በደቡብ ኢትዮጵያ አጥማቂው በአዞ ተገደሉ

ጌታያውቃል የሟች ቤተሰቦችን እንዴት ሊያሳምናቸው ቻለ?

ወ/ሮ ዘነቡ አመንቴ የሟች በላይ ቢፍቱ ባለቤት ናቸው። አቶ ጌታያውቃል የተባለው ግለሰብ እንዴት ወደ ቤት እንደመጣና ከዚያ በኋላ ስለተከሰተው ሁኔታ ይተርካሉ።

"ለቅሶ ሊደርሰን መጣ። እጁን አስታጥበነው የቀረበለትን ምግብ በላ። ከዚያም 'የማስተላልፈው መልእክት አለኝ' አለን።'' ካሉ በኋላ ሰውየው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአላዛርን ታሪክ ማንበብ መጀመሩን ያስታውሳሉ።

'በላይ ከሞት ይነሳል እዚህ ቤት ውስጥ ያላችሁ ሁሉ ጸልዩ' ማለቱን ጭምር።

ወይዘሮ ዘነቡ እንዳሉት መጀመርያ 'በላይ ከሞት ይነሳል ብላችሁ ታምናለችሁ ወይ?' ብሎ እንደጠየቃቸውና እነርሱም "አዎ እናምናለን" ብለው እንደመለሱለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"'በላይ ከሞት ይነሳል! ኑ ተከተሉኝ!' ብሎ ወደ መቃብር ሥፍራ ሲወስደን እኛም በላይ ከሞት ይነሳል ብለን አምነን ስለነበር በጣም ተደስተን እልል እያልን ተከተልነው።" በማለት ወ/ሮ ዘነቡ ሁኔታውን ዘርዘር አድርገው ያስረዳሉ።

''በቦታው ስንደርስ ሃውልቱን የሚገነቡት ወጣቶች ነበሩ። እነሱንም ሥራቸውን አስቆማቸውና መቃብሩ ላይ የነበረውን ድንጋይ ማንሳት ጀመረ፤ እኔ በወቅቱ ተንበርክኬ እየጸለይኩ ሳለው መቆጣጠር አቅቶኝ እራሴን ሳትኩኝ።'' የሚሉት ወ/ሮ ዘነቡ፤ ''ጉድጓዱ ተቆፍሮ፣ የሬሳ ሳጥኑ ተከፍቶ፣ አስክሬኑ የለበሰውን ሸራ ከላዩ ላይ አንስቶ 'በላይ ተነስ! በላይ ተነስ!' እያለ ሲጮህ ሰምቼ በድንጋጤ ከተኛሁበት ነቃሁ።'' ብለውናል።

መምህር ገቢሳ ቢፍቱ ደግሞ የሟች በላይ ቢፍቱ ታላቅ ወንድም ናቸው።

''ወደ መቃብሩ ሥፍራ የደረስኩት ጉድጓዱ ቆፍሮ የበላይን ስም እየጠራ ተነስ እያለ ሲጮህ ነው'' የሚሉት መምህር ገቢሳ ''በሁኔታው በጣም ማዘናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እናቴ እኔ እና እሱን ብቻ ነው የወለደችው። የታናሽ ወንድሜ አስክሬን እንደዛ ሲንገላታ ማየት በጣም ልብ የሚሰብር ነገር ነው'' ሲሉ የተሰማቸውን ይገልጻሉ።

ወ/ሮ ዘነቡ የባለቤታቸውን ሬሳ ሲመለከቱ ራሳቸውን ከሳቱ በኋላ የነቁት በሕክምና ተቋም ውስጥ ነበር''

በተለይም ሁለት ሕጻናት ልጆቻቸው የአባታቸውን አስክሬን በዛ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ማየታቸው እጅጉን እንደረበሻቸው ነግረውናል።

እራሱን 'ነብይ' ብሎ የሚጠራው አቶ ጌታያውቃል በቁጥጥር ሥር የሚገኝ ሲሆን ፍርድ ቤት ቀርቦ ቃል ስለመስጠቱ ከሟች ቤተሰቦች ሰምተናል።

አቶ ጌታያውቃል የወረዳው የጤና ቢሮ ባልደረባ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ