ከ48 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን በዓለም ዋንጫ የወከሉት አለም አቀፍ ዳኛው ባምላክ

ኡራጋይ ከ ሩሲያ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Sergei Fadeichev

ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው መሳተፍ ባይችሉም፤ ሁለት ኢትዮጵያውያን ግን በሙያቸው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በመዳኘት አገራቸውን በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ወክለዋል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ በዳኘነት የተሳተፉትአለም አቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማ ናቸው።

አለም አቀፍ ዳኛው ባምላክ ከእግር ኳስ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከብዙ ኢትዮጰያውያን የሚለይ አይደለም።

በልጅነታቸው እግር ኳስ በመጫወት ነው ያደጉት።

"የነበረኝ የእግር ኳስ ችሎታ እምብዛም ስላልነበረ ለክለብ ለመጫወት የነበረኝን ምኞት ማሳካት አልቻልኩም። ይህ ማለት ግን ለክለብ ለመጫወት የተለያዩ ሙከራዎችን አላደረኩም ማለት አይደለም።'' ይላሉ።

ከዚህም መካከል ለመብራት ኃይል ሲ ቡድን ለመጫወት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም ። በክለብ ደረጃ መጫወት ባይችሉም ለትምህርት ቤታቸው ቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተሰፈው እንደተጫወቱ ይናገራሉ።

በሰፈር ውስጥ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ከመጫወት በተጨማሪ የመሃል ዳኝነትን ሚና መውሰድ የጀመሩት።

በአዲስ አበባ ከተማ የዳኞች ስልጠና ላይ ተሳትፈው የዳኝነት ፍቃድን ካገኙ በኋላ የተለያዩ ውድድሮችን መዳኘት ጀመሩ።

የዓለም አቀፍ የዳኝነት ፍቃድ አግኝተው ላለፉት 9 ዓመታት በአለም አቀፍ ዳኝነት ደረጃ እየሰሩ ይገኛሉ።

አለም አቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማ የእግር ኳስ ዳኝነታቸው በተጨማሪ የነርሲንግ ሙያ ተመራቂ ሲሆኑ በህክምና ሙያ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የጤና ተቋም ውስጥ ሃኪም ሆነው አገልግለዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሾሎጂ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን በአንድ የጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ረዳት ተመራማሪ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, FABRICE COFFRINI

የሩሲያው የዓለም ዋንጫ

በሩሲያው 2018 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ከተመረጡ 6 አፍሪካዊያን ዳኞች መካከል አለም አቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማ አንዱ ነበሩ።

በአጠቃላይ ውድድሩን እንዲያጫውቱ ከተመረጡ 35 ዳኞች መካከል ባምላክን ጨምሮ 7 ዳኞች የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንዲዳኙ የተጠባባቂነት ሚና ተሰጥቷቸው ነበር።

በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ባምላክ የፈጸሙት እንድ ተግባር የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ሰቦ ነበር።

እሱም ሴንጋላዊው በመሃል ዳኝነት ሲመሩት በነበረው ሰርቢያን ከኮስታሪካ ባገናኘው ጨዋታ ላይ ተጠባባቂ ዳኛ የነበሩበት ግጥሚያ ነበር።

የጨዋታው ፍጻሜ ተቃርቦ ባለበት ሰዓት የሰርቢያው አምበል ከሜዳ ውጪ የወጣውን ኳስ በፍጥነት ወደ ሜዳ በመመለስ ጨዋታውን ለማስጀመር በሚጥርበት ወቅት የተቀናቃኝ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ተጨዋቹ ኳሷን እንዳያገኝ ሲከላከሉ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ወጥረት ነገሰ።

ባምላክ እንደሚሉት በየትኛውም ጨዋታ ላይ ከዳኛ ሃላፊነቶች መካከል አንዱ በተጨዋቾች መካከል ከበባና ግርግር አንዳይፈጠር ማድረግ ነው።

"እኔም ከመሃል ዳኛው ጋር በመሆን ይህን እንዳይሆን አድርገናል። ግርግሩን ማስቆም ባንችል ኖሮ በርካታ ቀይ ካርዶች ይመዘዙ ነበር። በውድድሩ መንፈስ ላይም መልካም ያልሆነ ነገርን ጥሎ የሚያልፍ ይሆን ነበረ'' ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ዳኛው ጨምረውም ከዚህ ጨዋታ በኋላ በነበራቸው ግምገማ ላይ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ከ48 ዓመታት በፊት በሜክስኮ የዓለም ዋንጫ ላይ ስዩም ታረቀኝ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ዳኛ ተሳታፊ እንደበሩም ባምላክ ይናገራሉ።

"ከረጅም ዓመታት በኋላ በዓለም ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን መወከል በመቻሌ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል። በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ በመቻሌ የዳኝነት ክህሎቴና ልምዴን ክፍ ማድረግ ችያለሁ''ይላሉ።

ባምላክ ከዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር በተጨማሪ ያለፉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ተሳትፈዋል፤ 2017 የካፍ ሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታን ዳኝተዋል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከኡራጓዩ አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬዝ እና ከሴኔጋሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ጋር ፊት ለፊት እንዳገናኛቸው የሚናገሩት አለም አቀፍ ዳኛው ፤ በዓለም ዋንጫው ላይ ተሳታፊ የነበሩት ዳኞችም የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ መድረክ መሳተፍ መቻላቸው ለሙያቸው ትልቅ እድል እንደነበር ይናገራሉ።

'ቫር' በዳኛው አተያይ

በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ እድገት በመጠቀበት ዳኞች ተንቀሳቃሽ ምስል ተመልክተው ውስኔ እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን አሰራር (ቪዲዮ አሲስታንት ሪፈሪ-ቫር) አንደኛው የእግር ኳስ አካል ሆኗል።

ይህንንም በተመለከተ ''ይህ በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነትጨዋታውን የበለጠ ፍትሃዊ እንዲሆን አስችሎታል'' ብለዋል።

ይህ አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ መተግበሩን የሚናገሩት ባምላክ "ይህም የእግር ኳስ ዳኝነትን እጅግ ከፍተኛ ሊባል በሚችል ደረጃ ፍትሃዊ ያደርገዋል እንዲሁም ዳኞች ስህተት እንዳይፈጽሙ ስለሚረዳቸው ወደፊትም በእግር ኳስ መድረኮች ጥቅም ላይ ቢውል መልካም ነው" ይላሉ።