የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የመደመር ጉዞ ወደ አሜሪካ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ ሐምሌ 18 ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ። በቆይታቸውም ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ።

እንደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ቢሮ ከሆነ ይሀ ጉብኝት የተሳካ እንዲሆን በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዋሽንግተን ከሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ እና ሎስ አንጀለስ ከሚገኘው የኢፌዲሪ ቆንስል ጄኔራል ጽ/ቤት ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው፡፡

ለዚህ ዝግጅትም የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ ባለሃብቶች በአጠቃላይ የተለያዩ የዳያስፖራ የህብረተሰብ ክፍሎች ደድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ቢሮው በፌስቡክ ገፁላይ አስፍሯል።

63 የሚሆኑ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከአዲስ አበባ የሄዱ የመገናኛ ብዙሃን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ሽፋን ለመስጠት ዝግጅት መማድረጋቸው ተገልጿል።

በዋሺንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆኑትና የዲሲው ግብረ ኃይል አባል የሆኑትን አቶ ቴዎድሮስ ካብት ይመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከዋሺንግተን ብቻ ሳይሆን ከዲሲ ሩቅ ከሆኑ ስፍራዎች በርካታ ቻርተርድ ባሶችን እየሞሉ ለመምጣት ያቀዱ እንዳሉም አስረድተዋል።

የሚመጣውን ሰው ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አዳራሽም መዘጋጀቱን ጨምረው ተናግረዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይነሳሉ ብለው ከጠቀሷቸው ጥያቄዎች መካከል ብሔርተኝነትን በተለይም ኢትዮጵያን በብሄር ከፋፍሎ ለመግዛት የሚደረገው ስልት ዛሬም ይቀጥላል ወይስ ያበቃል የሚሉ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ከጥያቄዎቹ መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

አሉላ ሰለሞን የዚህ ዝግጅት ኮሚቴ አባል ነው። አጠቃላይ ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ክብርና ድጋፍ የሚገልፅበት መድረክ ይሆናል ብሎ ያምናል።

ውይይቱ በቀጣይም የሚኖረው ፋይዳን የተጠየቁት አቶ አሉላ ብዙ መፈታት ያለባቸው ውስብስብ ጥያቄዎች አሉ ዲሞክራሲን ከማስፋት፣ የህዝብ ተሳትፎን ከማስፋት፣ ፍትሃዊ ምርጫን ከማካሄድ ጋር የተያያዙ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ የዳያስፖራ ክፍሎች አሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

በተለያየ የመገናኛ ብዙሃንም በአክቲቪስትነት የሚታወቁ ብዙ ሰዎች ይህንን ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ገልፀው የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ትክክለኛ የሆነ ለሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች መወዳደሪያ እና መዘጋጃ እድል እንዲኖር የሚጠይቁ ኃይሎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል መንግስት ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰተው ምላሽ ወደፊት የሚታእ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በአሜሪካ እስከ ሃምሌ 24 ድረስ በአሜሪካ ቆይታ ያደርጋሉ ተብሏል።