ጂቡቲ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብን የማንሳት ጥያቄ ተቃወመች

የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ

ለባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተፋጠው የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም መምጣት ተከትሎ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካም መልኩን እየቀየረ ነው።

ለአመታት ማዕቀብ እንዲጣልባት ግፊት ስታደርግ የነበረችው ኢትዮጵያ ማዕቀቡ እንዲነሳ የተባበሩት መንግሥታትን ጠይቃለች።

ከዚህም በተጨማሪ በውክልና ጦርነት የተሳተፉባት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ባለፈው ሳምንት ለሦስት ቀናት የኤርትራ ጉብኝታቸውን ተከትሎ በተመሳሳይ መልኩ ማእቀቡን እንዲነሳ መጠየቃቸው በጂቡቲ በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በኤርትራ ጉብኝታቸው ወቅት "የአፍሪካ ቀንድ ሃገራትን ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን እውን እንዲሆን ለማስቻል በኤርትራ ሕዝብ ላይ የተጣሉ ምዕቀቦችና ዕገዳዎች ሊነሱ ይገባል" ሲሉ ተናገግረው ነበር።

ጅቡቲ በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ

የዚምባብዌ የምርጫ ውጤት መገለጹን ተከትሎ አለመረጋጋት ሰፍኗል

ዶክተር ብርሃኑ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ምን ተወያዩ?

ጂቡቲ፤ ለረጅም ጊዜ የቆየ የድንበር ውዝግብ ላይ ከምትገኘው ከኤርትራ ጋር ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት ያላትን ፍላጎት ብትቀበለውም የማዕቀብ ማንሳት ጥያቄው ግን አስቆጥቷታል።

ሞቃዲሾ የሚገኘው የጂቡቲ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ውሳኔውን አስደንጋጭ ያለችው ሲሆን ጂቡቲያዊያን ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ሠላም በመጠበቅ ላይ ተሰማርተው ባሉበት ሰዓት መሆኑ ደግሞ በጭራሽ እንደማይቀበሉት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የጂቡቲ ተቃውሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ቀንድ የምታደርገው የኃይል ተፅእኖ ፈጣሪነት ጋር የሚገናኝ እንደሆነ የአፍሪካ ቀንድ ምሁሩ ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ ይናገራሉ።

በጂቡቲና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ከሁለት ዓመታት በፊት በተፈጠረ ቅራኔ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስና በጂቡቲ ወደብ ባለስልጣናት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የጂቡቲን ወደብ መጠቀም አቁማ ወደ ኤርትራ ፊቷን አዙራለች።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጂቡቲ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን የኃይል ተፅእኖ ስትቃወመው እንደነበር ይናገራሉ።

አረብ ኤምሬትስ ከጂቡቲ ጋር ያላት ቅራኔ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ"ተፅእኖ ፈጣሪነት ወይም የፖለቲካ ልዪነት የፈጠረው አይደለም። ኢኮኖሚያዊ ነው። ጂቡቲ ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ አፍስሳ ዱባይን የሚገዳደር የወደብ አቅም በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ነው" ይላሉ

ይህም ሁኔታ በቀጠናው ዘንድ የጦር ሰፈር በመመስረትም ሆነ አጠቃላይ አካባቢውን ለመቆጣጠር በምትፈልገው አረብ ኤምሬትስ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ይገልፃሉ።

"ኢትዮጵያና ሶማሊያ የኤርትራ ማዕቀብ እንዲነሳ መወትወታቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተፅእኖ የፈጠረውና ተቀጥላ በመሆን ነው ጂቡቲ ትላለች። የፀጥታ ፣ የኢኮኖሚ፣ የጂኦግራፊ ቁርኝት ካገሮቹ ከመኖሩ አንፃር የጂቡቲን ብሔራዊ ደህንነት ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ መወሰናቸው ልክ አይደለም። ይህ አግባብ ያለው ቅሬታ ነው" ይላሉ።

የባህረ ሰላጤው የአፍሪካ ቀንድን የመቀራመት ፍላጎት እየተጋጋመ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የኃይል አሰላለፉም እንደተቀየረ ፕሮፌሰር መድኃኔ ይናገራሉ

"የውጭ ኃይሎች ተፅእኗቸው የጨመረበት የአካባቢው አገሮችና መንግሥታት የራሳቸው ነፃ የሆነ ብሔራዊና ደህንነታቸውን የሚያስከብርላቸው የደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያራምዱበት እድል እየመነመነ መጥቷል" ይላሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ