በኢትዮጵያ የመንጋ ፍትህ የሰው ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል

የወደመ ንብረት

ባለፉት ሁለት ሦስት ቀናት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም የመንጋ ፍትህ ከህግ የበላይነት አንፃር ምን አይነት አደጋዎች እንደተጋረጡ አመላካች ነው።

በምስራቅ ወለጋ ወሊጋልቴ ገጠር ቀበሌም ቅዳሜ እለት ማምሻውን ሁለት ግለሰቦች በቡድን በድንጋይ ተደብድበው መሞታቸው ተሰምቷል።

እሁድ ደግሞ በሻሸመኔ ቦምብ ይዟል በሚል አንድ ሰውን ወጣቶች የስልክ እንጨት ላይ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለዋል።

ትላንት ጀዋር መሀመድን ለመቀበል በርካቶች በሻሸመኔ ከተማ ስታዲየም ተገኝተው ነበር።

በህዝብ መጨናነቅ ሳቢያ በተከሰተው መገፋፋት ሶስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉም አሉ።

የብዙሀኑ መነጋገሪያ የነበረው ግን ተደብዶቦ ህይወቱ ያለፈና ልብሱ ተገፎ፣ ተዘቅዝቆ የተሰቀለው ሰው ነው።

ግለሰቡ ማንም ቢሆን፣ ምንም አይነት ተግባር ቢፈጽምም የደረሰበት አሰቃቂ ጥቃት ኢ-ፍትሀዊ ነው የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠዋል።

አንድን ሰው በአንድ ወንጀል ከሶ፣ ራስ ምስክር፣ ራስ ፈራጅ፣ ቀጪም ራስ የሆነበት የደቦ ፍትህ በሻሸመኔ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም እየተስተዋለ ነው።

በሻሸመኔ ከተማ ጀዋርን ለመቀበል ወደ ስታዲየሙ አቅንተው ከነበሩ መካከል ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን ግለሰብ ግርግር ካየ በኃላ ነበር ስለ ክስተቱ የሰማው።

"ቦንብ ይዟል" የተባለው ሰው ተሰቅሎ የተመለከተ ሲሆን ተግባሩን "ትልቅ ስህተት" ይለዋል።

ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ማሰብና ከመሰል እርምጃ መቆጠብ እንዳለበትም ይናገራል። ሰው ተሰቅሎ ማየቱ እጅግ የዘገነነው ግለሰብ "አስጸያፊ ነው። በሀገራችን በባህላችንም የለም። ፍትሀዊም አይደደለም" ብሏል።

የሻሸመኔ ከተማ የፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር መኮንን ታደሰ እንደሚሉት ከድርጊቱ ጀርባ ያሉትን ግለሰቦችና ምክንያታቸውን በመጣራት ላይ ነው። ግለሰቡ "ሳንጃ ይዟል" የሚል ወሬ ተሰራጭቶ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ምንም መሳሪያ እንዳላገኘም ገልጸዋል።

ቅዳሜ እህል ጭኖ ወደ ትግራይ ክልል ይጓዝ የነበረ ተሳቢ አማራ ክልል ውስጥ በወጣቶች እንዲቆም ተደርጎ ጭነቱ መዘረፉም ተሰምቷል።

አሁን ነገሩ አስከፊ ደረጃ ላይ ቢደርስም ባለፉት የተወሰኑ ሳምንታትም በመንጋ ሰዎችን ማጥቃት እንዲሁም ንብረት ማውደም በተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋለ እውነታ ነው።

ከተወሰኑ ቀናት በፊት በአማራ ክልል አዊ ዞን በጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት አቅራቢያ በምትገኘው ፈንድቃ ከተማ ጥቃት ደርሶባቸው የሞቱትን የትግራይ ተወላጆች መጥቀስ ይቻላል።

ከዚያም በደሴ ከተማ ወጣቶች የተፈረደበትንና በህግ አስከባሪዎች ጥበቃ ስር መንገድ ላይ የነበረን ወንጀለኛ የቡድን ጥቃት በመሰንዘር ማስመለጣቸውን የአንደኛ ፓሊስ ጣቢያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ብሔርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ህይወት ሲጠፋ በርካቶች የእኛ ያሉት መኖሪያቸውን ጥለው ሊሰደዱ ግድ ሆኗል። የሚራራ ልብ ጠፍቶ ህፃናት እንኳ የዚህ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ታይቷል።

በሃዋሳ እንዲሁም በአሶሳ በተመሳሳይ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡም ጥቂት አይደሉም። ሰዎች በደቦ በድንጋይ ተወግረው፣ በዱላና በብረት ተቀጥቅጠው ህይወታቸውን ሲያጡ አጋጥሟል።

የዚህ ወገን የዚያኛው ወገን እየተባሉ በተለያዩ ቦታዎች መኪኖች ተቃጥለዋል ህንፃዎች በደቦ ወድመዋል። መንገዶችም በተደጋጋሚ ተዘግተዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰዎች በቡድን ተነስተው በሚወስዱት እርምጃ ህይወት እየጠፋ ንብረት እየወደመ ያለበት ሁኔታ ወደ አስከፊነት እየተሸጋገረ ነው የሚሉም አለ።

የማህበራዊ ሳይንስና የህግ ባለሙያዎች በዚህ ሁኔታ ሰዎች ራሳቸው ከሳሽ እራሳቸው ፈራጅም የሆኑበት ነው ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ትምህርት ክፍል ለ36 ዓመታት ያስተማሩት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ የመንጋ ፍትህ በእንግሊዝኛው 'ሞብ' የሚባለው ታፍኖ የነበረ ወይም ታፍኜ ነበር ብሎ የሚያስብ ማህበረሰብ አሁን ነፃ ነኝ ምንም የምሰራው ነገር አያስጠይቀኝም ብሎ ሲያስብ የሚገባበት ሁኔታ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ስለዚህም ሰዎች በግለሰብ አስተሳሰባቸው ሳይሆን በመንጋ ህሊና እየተመሩ ነው ይላሉ።

"አንድ ሰው በ'ሞብ' ሲሳፈር የሚመራው በራሱ ህሊና ሳይሆን በመንጋ ነው። መንጋው የራሱ ህሊና ይፈጥራል" የሚሉት ዶ/ር የራስ ወርቅ በመንጋ ህሊና ከፍተኛ ጥፋት ካደረሱ በኋላ ሰዎች ከመንጋው ተነጥለው ወደ ቤታቸው ሲሄዱና ወደ ህሊናቸው ሲመለሱ ያደረጉትን ማመን ሁሉ እንደሚከብዳቸውና ፀፀት እንደሚገባቸው በጥናት መመልከቱን ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለው የሚነገርለት ጀዋር መሃመድ፤ በአሁኑ ወቅት እዚም እዚያም እየታየ ያለው ጥቃትና ግጭት ከአምባገነን ወደ ደሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚደረግ ሽግግር ወቅት ክፍተት የሚፈጠር እንደሆነ ያመለክታል።

ጀዋር እንደሚለው ጊዜው የሽግግርና ክፍተት ያለበት ነው። ሰዎች ጠመንጃ የሚፈሩበት አይደለም የሕግ ሥርዓት ደግሞ እንደሚገባው እየሄደ አይደለም። ይህ ክፍተት ደግሞ "ሥርዓትና ህግ አልበኝነትን ይፈጥራል" ይላል።

ይህ ክፍተት በአፋጣኝ የማይሞላ ከሆነ ሽግግሩ በርግጥም ወደ ዲሞክራሲ ያመራል ወይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ጥያቄ ብቻም ሳይሆን በዚህ የሽግግር በሚባለው ጊዜ የሚታዩ የደቦ ጥቃትና ንብረት ማውደሞች በጥቅሉ ሥርዓት አልበኝነትን በማጤን ነገሮች ወዴት እያመሩ ነው በሚል ስጋት ያደረባቸውም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ ሁሉ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ እንደሆነ ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩም አሉ።

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ነገሮች ከባድ እንደሚሆኑና እስካሁን የተከፈለውም ዋጋ ከባድ እንደሆነ ዶ/ር የራስ ወርቅ ይናገራሉ። "የሆነው ሆኗል ለወደፊት እንዳይሆን ብንል እንኳ እስካሁን የተደረገው የራሱ ጠባሳ ይኖረዋል። በተለይም በሃይማኖትና በብሔር የሚደረጉ ጥቃቶች የሚያገረሹ ናቸው" ብለዋል።

ዶ/ር የራስ ወርቅ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ ሲገልፁ ጀዋር ደግሞ ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ይፈልጋል በማለት ሃሳብ ይሰነዝራል።

በደቦ በመንቀሳቀስ ሳይሆን ህብረተሰቡ በአካባቢው ከፖሊስና ከአካባቢ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ነገሮችን ማረጋጋት እንደሚገባ በብሔራዊ ደረጃም ግን አፋጣኝ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ጀዋር ይናገራል።

"ችግሩ ፈጣን የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልገዋል። ይህ ማለት ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በመቀራረብ ህዝብን ሊያሳምን የሚችል ህግጋትን ማውጣት አለባቸው" በማለት ይደመድማል።