በድሬዳዋ ከተማ በተከሰተ ግጭት የ10 ሰዎች ህይወት ጠፋ

የታይዋን ገበያ ከፊል ገፅታ-ድሬዳዋ

ትናንት እሁድ በድሬዳዋ ከተማ ብሔርን የለየ ግጭት ተከስቶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ቢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች እንደሚሉት ግጭቱ የተቀሰቀሰው በኦሮሞዎችና በሶማሌዎች መካከል እንደሆነ ገልፀዋል።

ትናንት ረፋድ ላይ ገንደ ገራዳ በሚባለው አካባቢ የጃዋር መሃመድን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አስመልክቶ የተሰባሰቡ ሰዎች ሲጨፍሩ አንደኛው ወገን ጥቃት ሊፈፀምብን ነው በሚል ያልተጣራ መረጃ ምክንያት መሆኑን ሰምቻለሁ ትላለች አንዲት የዓይን እማኝ።

"ከዚያ በኋላ የነበረው ሁኔታ በጣም ከባድ ነበር፤ ዘር እየተለየ ነው የዱላና የድንጋይ እሩምታ የነበረው፤ ሁሉ ነገር ድብልቅልቅ ያለ ነበር " ብላለች።

ከዚህም በተጨማሪ ቤቶች ሲቃጠሉና መመልከቷንና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ማየቷን ተናግራለች።

የደቦ ጥቃቱ በተለይም ቁጠባ፣ ፖሊስ መሬት፣ ሼክ ሃቢብ፣ ገንደ ገራዳና ቢላል ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከአንዱ ወደሌላው እየተዛመተ ሄዶ ነበር ።

ኦሮሞና ሶማሌዎች እርስ በእርስ እንጂ ማናቸውም ቢሆን ሌላ ብሄርን አላጠቁም ብትልም ግጭቱ በማን ፍላጎት እየተካሄደ እንዳለ ግን መለየት አስቸጋሪ ሆኖባታል።

"እኛ ከጎናችንም ከፊታችን ኦሮሞዎችም ሶማሌዎችም አሉ፤ ጎረምሶቹም አዋቂዎቹም አንድ ላይ ቆመው እያወሩ ነው፤ ከየት አካባቢ የመጣው ሰው ጸብ እንደሚፈልግ ራሱ ግራ ነው የሚያጋባው"

ሌላኛው የዓይን እማኝ ገንደ ገራ፣ ፖሊስ መሬት፣ ቁጠባ፣ አዲስ ኬላ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በአካባቢዎቹ በመስፈር በቡድን ተደራጅተው ለጸብ የሚወጡ ወጣቶችን ለመበተን የአስለቃሽ ጋዝ መልቀቃቸውን ነግሮናል።

አክሎም በዚህ ግጭት እስካሁን ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ሲናገር ሌላዋ ወጣት ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር አምስት ብቻ ነው ትላለች።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዲፂዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን ባንታለም ግርማ በበኩላቸው በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 09 አንዳንድ መንደሮች ላይ ግጭቱ እንደተጀመረ ተናግረዋል።

በከተማዋ ውስጥ በነበረው ግጭት በደረሰ ቃጠሎ የአስር ሰዎች ህይወት ማለፉን የተናገሩት የፀጥታ ኃይሉ ግጭቱን ለማብረድ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የግጭቱ መንስኤ ፖሊስ እያጣራ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው የከተማው አስተዳደር የብሄር መልክ እንደሌለው እንደሚያምን ገልፀዋል። ነገር ግን አንዳንዶች የብሔር መልክ ለማስያዝ እንደሞከሩም አስረድተዋል።