በሶማሌ ክልል የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ድብደባና ግድያ ተፈፅሟል

የጅጅጋ ከተማ ከፊል ገፅታ

የፎቶው ባለመብት, Cakaara News

ጂግጂጋ ውስጥ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በተለዩ ሰዎችና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃት እንደደረሰ የአብያተ ክርስቲያናቱ ተወካዮች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት የጅግጅጋ ወረዳ ቤተ-ከህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ኢዮብ ወንድሙ በክልሉ ሰባት ካህናት መገደላቸውንና ሰባት አብያተ-ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጂግጂጋ ወንጌላዊያን አብያተ-ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ ፓስተር ጋሻው ገ/ዮሃንስ በበኩላቸው እንደተናገሩ ወደ አስር የሚጠጉ አብያተ-ክርስቲያናት የዘረፋ እና እሳት ቃጠሎ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንዶቹ አብያተ-ክርስትያናት ውስጥ በአምልኮ ሥርዓት ላይ የነበሩ አገልጋዮችና አማኞች ተደብድበዋል። ሊቀ ካህናት ኢዮብ አክለውም እስካሁን ትክክለኛው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

ከተቃጠሉት የኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት ውስጥ በጂግጂጋ ከተማ በ7 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ በቅርቡ የተመረቀው የምሥራቀ-ፀሐይ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ካቴድራልም ይገኝበታል።

"በዚሁ ግቢ ውስጥ ወደ ሦስት ሰዎች ሞተው እስከሬናቸው ተቃጥሏል፤ አንዱን ጭራሽ መለየትም አልቻልንም። በቅድስት አርሴማም አንድ መሪ ጌታ ሞቶብናል" ብለዋል ሊቀ ካህናት ኢዮብ።

አክለውም የሊቀ-ጳጳሱ መኖሪያም (መንበረ ጵጵስና) በርና መስኮቱ ተገነጣጥለው እያንዳንዱ እቃ መወሰዱንና ምንም የቀረ ነገር አንደሌለ ነው የተናገሩት። ሊቀ-ጳጳሱ በወቅቱ ለቤተ-ክርስቲያኒቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ነበሩ።

"መውሰድ የሚችሉትን ወስደው ያልቻሉትን ደግሞ አቃጥለው ነው የሄዱት።"

ከግድያው በተጨማሪ የእርሳቸውንም ጨምሮ የበርካታ ምዕመናን ቤት እየተሰበረ ዘረፋ መፈጸሙንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በክልሉ በተፈጸመው ድርጊት ሳቢያ የሰው ህይወት በመጥፋቱ ሃዘናቸውን መግለፃቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ብፁዕነታቸው ሰባት አብያተ-ክርስትያናት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው የካህናት ህይወት ማለፉንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፤ በሁኔታው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

ሊቀካህናት ኢዮብ አንድሚሉት በጂግጂጋ ከተማ በሰበካ ጉባኤ አባልነት ሰላሳ ሺህ ምዕመናን ተመዝግበዋል።