በጅግጅጋ ግጭት ሸሽተው የተሸሸጉ ሰዎች በከፋ ችግር ላይ ናቸው ተባለ

ጅግጅጋ Image copyright BBC Somali

በጂግጂጋ ከተማ ዛሬም የክልሉ ልዩ ኃይልና ከሚፈፀሙ ጥቃቶች ሸሽተው በተሸሸጉ ወገኖች መካከል ግጭት መፈጠሩን የዓይን ዕማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን የደበቁ አንድ የረድኤት ድርጅት ባልደረባ ዛሬ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና ግብረሰናይ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች እና የሀገር ሸማግሌዎች ወደ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ኦማር በማቅናት መወያየታቸውን ገልፀዋል።

በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ችግሩ የተፈጠረው የፌዴራል መንግሥት ወታደሮች በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ጨምረውም ቅዳሜ ዕለት በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን ገልፀው፤ ጥፋትና ውድመት ያስከተሉት «የአክራሪ እስልምና ቡድኖች» መሆናቸውንና ህዝቦች አሁንም በወንድማማችነት እንዲኖሩ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ እንደነገሯቸው አጋርተውናል።

ተወካዮቹ በየአብያተ-ክርስቲያናቱ የተጠጉ ወገኖች በረሃብ እና እርዛት ውስጥ መሆናቸውን በመናገር የሚቀመስ ምግብ የክልሉ መንግሥት ማደል እንዲጀምር በጠየቁት መሰረት ዳቦ፣ ተምር እና ውሃ በመኪና ተጭኖ በየአብያተ-ክርስቲያናቱ ተጓጉዟል።

ሆኖም በከተማው ቀበሌ 06 በሚገኘው መሠረተ-ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ ወጣቶችና የክልሉ ልዩ ኃይል በምግብ ዕደላው ወቅት መጋጨታቸውን ገልፀዋል።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የዓይን እማኙ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በከፈቱት የሩምታ ተኩስ ሦስት ወጣቶች ተመትተው ሲወድቁ ማየታቸውን ተናግረው ቢቢሲም በስፍራው ካሉ ሰዎች ይህንን ለማረጋገጥ ችሏል።

የረድኤት ድርጅት ሠራተኛ የሆኑት የዓይን እማኝ እንደሚሉት የተመለከቱት የምግብ እጥረት አሳሳቢ መሆኑን ሲጠቁሙ «ጥሬ ማንጎ ለመብላት የሚንሰፈሰፉ ሰዎችን በዓይኔ አይቻለሁ ብለዋል።

የሸሹ ሰዎች ተጠልለውባቸው የሚገኙ አብያተ-ክርስቲኣናትን የተመለከቱ ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ ነፍሰጡሮችና ሕፃናት በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ከከተማዋ ለመውጣት ያልቻሉና ተሸሽገው የሚላስ የሚቀመስ ያጡ ወገኖች የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑንም የዓይን እማኞቹ አክለው ተናግረዋል።

የሚመለከታቸውን የክልሉ ኅላፊዎች በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ