የሃገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር ታዘዘ

የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር ታዘዘ።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ እንዳሉት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጥያቄ መሰረት የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ የጸጥታ ማስከበር ሥራ ይሰራሉ።

በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ፀጥታ የማስከበር ስራ እንደሚጀምር የጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሺዴ ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ከ10 የሚበልጡ አብያተ ክርስትያናት ጥቃት ደረሰባቸው

በሶማሌ ክልል በተከሰተ ቀውስ ህይወት ሲጠፋ አብያተ-ክርስትያናት ተቃጠሉ

ቀደም ሲል የሶማሌ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊ ኢድሪስ እስማኤል አብዲ ለቢቢሲ ሶማሊኛ እንደተናገሩት "ፌዴራሊዝምን መሰረት ያደረገ ህገ-መንግሥት አለን። በህገ-መንግሥቱም መሰረት የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ የሚገባው ከክልሉ አቅም በላይ ሲሆንና በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት ነው። የመከላከያ ሰራዊት ህገ-ወጥ በሆነና ከህገ-መንግሥቱ በሚፃረር መልኩ እኛን ሳንጠይቅ ገብቷል። ለጊዜው መገንጠል አላሰብንም በፌደራል ሥርዓቱም እንተዳደራለን፤ ነገር ግን መገንጠል መጥፎ ሀሳብ አይደለም። ህገ-መንግሥቱም ለዛ ዋስትና ሰጥቶናል" በማለት ተናግረው ነበር።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በሶማሌ ክልል የሚገኙ ትውለደ ሶማሌ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት እየተሰነዘረ መሆኑ በስፋት የተዘገበ ሲሆን፤ በርካቶችም የድረሱልን ጥሪ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

በጅግጅጋ ግጭት ሸሽተው የተሸሸጉ ሰዎች በከፋ ችግር ላይ ናቸው ተባለ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተከሰተውን ሁከት ለማስቆም ከሁለት ቀናት በፊት የሃገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቆ ነበር።

የተከሰተው ብጥብጥ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሻገር ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞች እየተዛመት መሆኑን በመጥቀስ ይህም ''በምንም አይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊገታ እና ሊታረም የሚገባው ድርጊት ነው" በማለት ነበር ሠራዊት መግለጫ አውጥቶ የነበረው።

ቅዳሜ ዕለት በሶማሌ ክልል በተቀሰቀሰው ሁከት የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የዕምነት ተቋማትን ጨምሮ በግለሰቦች ንብረት እና በባንኮች ላይ ዝርፊያ እና በእሳት የማውደም ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ