አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከስልጣናቸው ወረዱ

አቶ አብዲ ሞሃመድ

የፎቶው ባለመብት, BBC Somali

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ኢድሪስ ኢስማኤል ለቢቢሲ ሶማልኛ አረጋግጠዋል።

ከኢድሪስ ኢስማኤል መረዳት እንደተቻለው፤ አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከክልሉ ፕሬዚዳንትነታቸው ይነሱ እንጂ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ሆነው ይቆያሉ።

ኢድሪስ ኢስማኤል ጨምረው እንደተናገሩት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የቀድሞውን ፕሬዝደንት በመተካት ተሹመዋል።

የምስሉ መግለጫ,

አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት አህመድ አብዲ ሞሃመድ

አዲሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የሶማሌ ክልል ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

አህመድ አብዲ ሞሃመድ አመሻሹን ከቢቢሲ ሶማልኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን አስረክበው በሰላም የስልጣን ሽግግር መካሄዱን ተናግረዋል።

አህመድ አብዲ ሞሃመድ ''አብዲ ሞሃመድ ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የክልሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዲስ መሪ መርጧል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ጂግጂጋ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ'' ሲሉም ተደምጠዋል።

ከቅዳሜ አንስቶ በጂግጂጋ እና በክልሉ ሌሎች ከተሞች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ የሃገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር መታዘዙ ከሰዓታት በፊት ይፋ ተደርጎ ነበር።

በስፋት ''አብዲ ኢሌ'' በመባል የሚታወቁት አብዲ ሞሃመድ ኡመር ስልጣን በፍቃዳቸው ወይም ተገደው ስለመልቀቃቸው የታወቀ ነገር የለም።

ባለፉት ሶስት ቀናት በክልሉ በተከሰተው ሁከት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት መውደሙም ተነግሯል።