"አብዲ ሞሃመድ ኡመር ስልጣን ለመልቀቅ በተደጋጋሚ ጠይቀው ነበር" አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት

አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አህመድ አብዲ መሀመድ

የፎቶው ባለመብት, BBC

የሶማሌ ክልል አዲሱ ፕሬዚዳንት አህመድ አብዲ መሀመድ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሀመድ ኦማር ስልጣን እንዳስረከቡና ሽግግሩም በሰላም እንደተጠናቀቀ ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።

የክልሉ አዲሱ ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ስልጣን ለመልቀቅ በመጠያቃቸው የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ አዲሱን የክልሉ ፕሬዚዳንት እንደመረጠም ገልፀዋል።

ሰሞኑን ለብዙ ሰዎች ሞት፣ ለአብያተ-ክርስትያናት መቃጠልና ንብረት መውደም ጋር ተያይዞም በክልሉ የመከላከያ ሠራዊት የገባ ሲሆን፤ በክልሉ በነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞም በማዕከላዊ መንግሥት ግፊት ምክንያት እንደወረዱ ብዙዎች አስተያታቸውን ቢሰጡም አዲሱ ፕሬዚዳንት ሲንከባለል የነበረ ጥያቄ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ስልጣን ለመልቀቅ ባለፈው አራት ዓመት ጥያቄ ቢያቀርቡም በፓርቲያቸው ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ነበር" ብለዋል። ጨምረውም በትናንትናው ዕለት ይህ ጥያቄ ተቀባይነት እንዳገኘም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጂግጂጋ በሚገኘው ቤታቸው ቤታቸው ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረው ምንም እንኳን የሥራ አስፈፃሚነትን ስልጣን ቢያስረክቡም የፓርቲያቸው ሶህዴፓ ኃላፊ ሆነው ይቆያሉ ብለዋል።