ታዋቂው ተከታታይ ፊልም ቢግ ባንግ ቲዎሪ ሊጠናቀቅ ነው

ቢግ ባንግ ቲዎሪ ሊጠናቀቅ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው ታዋቂ የቲቪ ተከታታይ ፊልም ቢግ ባንግ ቲዎሪ በአውሮፓውያኑ ቀጣይ አመት ይጠናቀቃል። በአሜሪካ ሲት ኮም ታሪክ ረዥም ክፍል ያለው ተብሏል።

የፊልሙ 12ኛና የመጨረሻ ክፍል በመስከረም ወር ተጀምሮ በመጋቢት ወርም ይጠናቀቃል ተብሏል።

መቼቱን በካሊፎርኒያ ፓሴዴና ያደረገው ይህ ፊልም በሁለት ዶክተሮችና የፊልም ተዋናይት ለመሆን በምትጥር ገፀ-ባህርያት ላይ የሚያጠነጥን አስቂኝ ፊልም ነው።

በአውሮፓውያኑ 2012 ስድስተኛው ክፍል መውጣቱን ተከትሎ 18 ሚሊዮን ተከታታዮችን ማፍራት ችሏል።

በያንዳንዷ ክፍልም 18.6 ሚሊዮን ተመልካቾች መኖሩን ያስመዘገበ ሲሆን፤ በአሜሪካም ትልቅ ተመልካችን ማፍራት የቻለ የቲቪ ፊልምም መሆን ችሏል።

የፊልሙ አዘጋጆች በጋራ በሰጡት መግለጫ "ለወዳጆቻችን ምስጋናን እናቀርባለን" ብለዋል።

ተከታታይ ፊልሙ ለአርባ ስድስት ግራሚዎች የታጨ ሲሆን ሼልደን ኩፐርን ወክሎ የሚጫወተው የፊልሙ መሪ ተዋናይ ጂም ፓርሰን አራት ሽልማቶችንም ተቀብሏል።

የሼልደን ገፀ-ባህርይ ታዋቂነትን ከማግኘቱ በተጨማሪ "ህፃኑ ሼልደን" (ያንግ ሼልደን) የሚል ተከታታይ ፊልም እንዲሰራ መነሻ ሆኗል።

የፊልሙ ሌሎች ተዋናዮች ጆኒ ጋሌስኪ፣ ሲሞን ሄልበርግ፣ ኩናል ናያርና ኬሊ ኩዎኮ ናቸው።

ከሁለት አመታት በፊትም ዋናዎቹ ተዋናዮች በአንድ ክፍል ትወና ብቻ አንድ ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏቸዋል።

ለተዋናዮቹ ከሚፍለውና ብዙ አመትም ከመታየቱ አንፃር ለማዘጋጀት በጣም ውድ ስለሆነ ነው 13ኛውን ክፍል ማዘጋጀት የተሳናቸው የሚሉ ግምቶችን ያስቀመጡ ሚዲያዎች አሉ።

የፊልሙን መቋጨት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ስሜቶችን አስተናግዷል።