ስቃይ የደረሰበት ኡጋንዳዊ ፖለቲከኛ ቦቢ ዋይን ተፈታ

ዑጋንዳዊው ታዋቂ ሰው ቦቢ ዋይን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከሙዚቃ ሕይወት ወደ ፖለቲካ ሕይወቱን ያዞረው ኡጋንዳዊው ታዋቂ ሰው ቦቢ ዋይን ከቀናት እሥር በኋላ በዋስ እንዲለቀቅ ሆኗል።

ቦቢ ዋይንን ጨምሮ ሌሎች በሃገር ክህደት የተከሰሱ 33 ኡጋንዳዊያን ናቸው ትላንት ከሰዓት በኋላ በዋስ የተለቀቁት።

'የደሃ መንደር ፕሬዝደንት' በሚል ቅፅል ስያሜ የሚታወቀው ቦቢ ዋይን ፍርድ ቤት የቀረበው በክራንች ድጋፍ ነበር።

ቦቢ ዋይንን በቁጥጥር ሥር ያዋለው የኡጋንዳ ወታደራዊ ኃይል ግለሰቡን አሰቃይቷል የሚለውን ክስ 'መሠረተ ቢስ' ሲል አጣጥሎታል።

በመዝገብ ስሙ ሮበርት ኪያጉላኒ በመባል የሚታወቀው ቦቢ ዋይን የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ነበር ለደጋፊዎቹ ንግግር እያደረገ ሳለ በቁጥጥር ሥር የዋለው።

ክስ ከተመሰረተባቸው ግለሰቦች መካከል አንድ የ51 ዓመት ግለሰብ ፍርድ ቤት ውስጥ ሳሉ ራሳቸውን መሳታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ለተወሰነ ሰዓት ያክል በአንድ እግሩ ቆሞ እንደነበር የቢቢሲዋ ካትከሪን ከስፍራው ዘግባለች።

ቦቢ ዋይን ለእሥር ከመዳረጉ በፊት «ይኸው እኔ መስያቸው ሹፌሬን ገደሉት» በማለት አንድ አሰቃቂ ፎቶ የትዊተር ገፁ ላይ ለጥፎ ነበር።

የግለሰቡ ጠበቃዎች ደንበኛችን ስቃይና እንግልት ደርሶበታል ቢሉም የሙሴቬኒ መንግሥት ግን ወቀሳውን 'ሃሰት' ብሎታል።

የተከለከለ የጦር መሣሪያ በመያዝ በሚል ክስ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲከሰስ ተፈርዶበት የነበረው ቦቢ ዋይን ኋላ ላይ ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ እንዲታይ ሆኖለታል፤ ክሱን የሃገር ክህደት በሚል ተቀይሯል።

የ36 ዓመቱ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይንን ጨምሮ ሌሎቹ ተከሳሾች በፈረንጆቹ ነሃሴ 30 ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።