ዘጠኝ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ታሰሩ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አለም አቀፍ በረራዎችን በማስተጓጎል የተጠረጠሩና የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ስራ ማቆም አድማ አስተባብረዋል የተባሉ 9 አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መታሰራቸውን ፌደራል ፖሊስን በመጥቀስ ፋና ዘግቧል።

አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ላይ እንደነበሩ ይታወቃል።

አድማውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር እንዲሁም የስራ ማቆም አድማውን ካስተባበሩ ሰራተኞች በጥቅሉ ዘጠኝ ባለሙያዎች ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮችና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር ድርድር ላይ እንደነበሩ ምንጮች ለቢቢሲ አማርኛ ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ፣ ባህር ዳርና መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የስራ ማቆም አድማ መትተው ነበር።

የትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ከደሞዝ ጭማሬ፣ ከስራ ምዘና ፣ እውቅናና ከጥቅማጥቅም ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነው ከላይ በተጠቀሱት አውሮፕላን ማረፊያዎች አድማ የመቱት።

ተመስገን ቂጤሳ በአዲስ አበባ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ነው። የነበረባቸውን አስተዳደራዊ ጫና ተቋቁመው ለሙያቸው የሚገባው እውቅና እንዲሰጥና ጥቅማጥቅም እንዲጠበቅ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን ለቢቢሲ ገልፆ ነበር።

ለጥያቄያቸው አለመመለስ መሰረታዊ ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነ ተናግሯል።

ተመስገን ባለስልጣኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ጥያቄ ለመመለስ ልሞክር የሚልበት መንገድ ሙያውን በትክክል ካለመረዳትና የሚገባውን እውቅና ካለመስጠት የሚነሳ እንደሆነ አስረድቷል።

"ዛሬ ላይ የተደረሰው በዚህ ምክንያት ነው" ብሏል።

በረራዎች በአድማው ምንም እንዳልተስተጓጎሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቢገልጽም ተመስገን ግን ክፍተቱን ለመሙላት የተሞከረው ከስራው ርቀው የቆዩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን እንዲሁም ስልጠናቸውን ያልጨረሱ ተቆጣጣሪዎችን በማሰማራት መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ገልፆ ነበር።

ድምፃቸውን ለማሰማት አስበው የነበረው ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመው ሳይሆን የተወሰኑ ስራዎችን ( ቪ አይ ፒ ፣ አምቡላንስ እና ወታደራዊ በራራዎችን) ብቻ እየሰሩ ከስራ ገበታቸው ላይ ሆነው እንደነበር ነገር ግን ጠዋት ላይ ወደ ስራ ቦታቸው ሲሄዱ እንዳይገቡ መደረጉን ተመስገን ተናግሯል።

ተመስገን እንደሚለው ከአድማው አንድ ቀን ቀደም ብሎም አንድ ፎርም እንዲሞሉ ፤ እሱን ካልሞሉ ግን የስራ ውላቸው እንደሚቋረጥ ማሳሰቢያም ተሰጥቷቸው ነበር።

አድማው መቼ እንደሚያበቃ የቀረበለትን ጥያቄ በማስመልከት "ከባለስልጣኑ በላይ እንዲሁም በለውጥ ላይ ያለ መንግሥት አለ እንዲሰማን እንፈልጋለን"ብሏል።

አስር እጥፍ ወይም 1 ሺህ በመቶ ደመወዝ ጭማሪ የጠየቃችሁት ደመወዛችሁ ስንት ቢሆን ነው? የሚልጥያቄ ለተመስገን አንስተን ነበር።

በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የአለም አቀፉን ስራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) ሰነድ የፈረመች አገር በመሆኗና ሰነዱም የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ካለባቸው የስራ ጫናና ስራው ከሚጠይቀው ሙያዊ አቅም አንፃር ከመርከብ ካፒቴን እንዲሁም ከኮሜርሻል ፓይለት እኩል እንዲከፈለው ማስቀመጡን ተመስገን ተናግሯል።

"አገሪቱ ለፓይለት ትከፍላለች ። እኛ የሚከፈለን ግን አንድ መካከለኛ ፓይለት ከሚከፈለው ከአንድ ሃያኛ ያነሰ ነው። ለምሳሌ እኔ ሰባት ዓመት ሰርቻለው የሚከፈለኝ በወር 380 ዶላር ነው። የምሰራው ስራ ግን ከዚህ በላይ ዋጋ ያወጣል። የማገኘው ሌላ ምንም ዓይነት ጥቅማጥቅም የለም።" በማለት ሁለተኛውን ነጥቡን ያስቀምጣል።

በሶስተኛ ደረጃ የሚያነሳው ነጥብ የጎረቤት አገር አየር መንገዶችን ተሞክሮ ነው። ''ኬንያ ከኢትዯጵያ ጋር ተመጣጣኝ ኢኮኖሚ ነው ያላት። የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከእኛ አምስት በመቶ እጥፍ ደመወዝ ያገኛሉ። ጥቅማጥቅም ሳይጨመር" በማለት ያለጥናት እንዲሁ አስር እጥፍ ይጨመርልን አለማለታቸውን አስረድቷል ተመስገን።

ያላግባባቸው ባለስልጣኑ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሙያን ሲመዝን ከዚህ ቀደም የሰራውን ጥናት መሰረት በማድረግ ጥያቄአቸውን ለመመለስ በመሞከሩ እንደነበርም ተመስገን ያስረዳል።

የኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው አቶ ፍፁም ጥላሁንም የባለሙያዎቹ ጥያቄ ከዓመታት በፊት በ45 ቀን ይመለሳል ተብሎ ስምንት ዓመታት እንዲሁ ማለፋቸውን ለቢቢሲ ገልፆ ነበር።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጀነራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው «እስከዛሬ ድረስ በመሰል ደረጃ የወጣ ጥያቄ አልነበረም» ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

«ከዚህ ቀደም የነበሩት ጥያቄዎች ከደረጃ አሰጣጥ (ሬቲንግ) ጋር የተያያዙ ነበሩ፤ እኒህ ጥያቄዎች ደግሞ በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት የሚመለሱ ናቸው። ለዚህ ኮሚቴ ተቋቁሞ እነሱንም የኮሚቴ አባል አድርገናቸዋል» በማለት ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁኔታውን አስረድተዋል።

«እውቅና የመስጠት ጉዳይም ሌላው ነገር ነው፤ በዚህ በኩል ደግሞ መንግሥት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ሥራ እውቅና በመስጠት በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ደሞዝ እየከፈለ ነው ያለው።» በማለት እዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት ያልተቻለው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ እውቅናን ከገንዘብ ጋር ስላያያዙት እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ።

«ሃገሪቱ ልትከፍል በምትችለው አቅም ጥናት አስደርገን ኮሚቴ አቋቁመን እነሱም የኮሚቴው አባል ሆነዋል። ነገር ግን እነሱ እየጠየቁ ያሉት 1 ሺህ በመቶ (አስር እጥፍ) የደሞዝ ጭማሪ ይደረግልን ነው።»ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም «ደመወዛችን አንሷል፤ መንግሥት እኛ በፈለግነው መጠን ካልከፈለን አድማ እንመታለን ብሎ መንግስትን ማስገደድ ተገቢ ነው ወይ? በሌላው ዓለምስ ይሄ ያስኬዳል ወይ?»በማለት ጥያቄም አንስተዋል።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ ላለፉት ዓመታት አለብን የሚሉትን ችግር ሲያሰሙ እንደነበር በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኃላፊው መንግሥት በሚያደርገው የደሞዝ ጭማሪ መሠረት ባለሙያዎቹ ተጠቃሚ ሲሆኑ እንደነበር ነገር ግን የ1 ሺህ በመቶ ጭማሬ ጉዳይ ሲነሳ ሲሰሙ የመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልፀዋል።

«ምንም እንኳ መንግሥት አንድ ሺህ በመቶ (አስር እጥፍ) የሚለውን ኃሳብ ባይቀበለውም በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ጥናት እያካሄደ ነው»

የባለሙያዎቹ አድማ መምታት በረራ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ካለ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው «በአድማው ተሳታፊ ያልሆኑ ባለሙያዎች ፣ ከዚህ ቀደም የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ የነበሩና በሌላ ስራ ላይ ተመድበው የነበሩ ሌሎች ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ እንዲሁም ባለሙያዎችን ከውጭ አገር አየር መንገዶች በማምጣት ሥራው ያለ አንዳች እንከን እንዲካሄድ እያደረግን ነው» በማለት መልስ ሰጥተዋል።

ይህ ዘላቂ መፍትሄ መሆን ይችላል ወይ ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ «እንግዲህ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ የደሞዝ ጭማሪ የጠየቀን ባለሙያ ሌላ የምንይዝበት መንገድ የለም፤ ሌላም አማራጭ የለም፤ ስለዚህ ይህ ብዙ ችግር አይሆንብንም» ብለዋል።