በዓመቱ ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት ለኢንስቨትመንት ደንቃራ ሆኖ ነበር ተባለ

ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
የምስሉ መግለጫ,

በ2010 የበጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ፍሰት 4.6 ቢሊዮን ለማምጣት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው መጠን ግን 3.75 ቢሊዮን ዶላር ነው

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ በፅሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ከአንድ ወር በፊት የተጠናቀቀው የ2010 የበጀት ዓመት ለኮሚሽኑ በብዙ ረገድ "በጣም ፈታኝ ግን ደግሞ ውጤታማ ነበር" ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋሉ ያለመረጋጋቶች በኢንቨስትመንት ላይ "ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል።" የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ዕቃን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት እና ማስወጣት ጋር በተያያዘ ያለው የማጓጓዣ ፍጥነት (ሎጅስቲክስ) ችግር ሌሎች ፈተናዎች ነበሩም ተብለው በኮሚሽነሩ ተጠቅሰዋል።

በሰኔ 16ቱ ፍንዳታ ጥቅም ላይ ከዋለው ቦምብ ጋር የሚመሳሰል ቦምብ በተጠርጣሪ ቤት ተገኘተፅዕኖው በኢንቨስትመንት ፍሰት ረገድ በቀዳሚው የ2009 የበጀት ዓመት ከነበረው በታየው መጠነኛ መቀነስ ይገለፃል የሚሉት ኮሚሽነሩ በተጠቀሰው ዓመት የነበረው የኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን 4.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደነበረ ያስታውሳሉ። በ2010 የበጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ፍሰት 4.6 ቢሊዮን ለማምጣት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው መጠን ግን 3.75 ቢሊዮን ዶላር ነው።እንደዚያም ቢሆን እንደኮሚሽነር በላቸው በዓመቱ ውስጥ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፤ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሥራ እንዲቀጥሉ በማገዝ እና መተማመንን በመፍጠር ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ270 በላይ የውጭ ባለሃብቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን ባለሃብቶቹ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ኢንቨስት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዓመቱ ኮምቦልቻ እና መቀሌ ፓርኮች ሥራ መጀመራቸው ከኮሚሽኑ ስኬቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ያወሱት ኮሚሽነር በላቸው አሁን በአገሪቱ ውስጥ ስራ በጀመሩ ስድስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሃምሳ ሃምስት ሺህ ለሚጠጉ ሠራተኞች ስራ ተፈጥሯል ብለዋል።

ኮሚሽኑ የማምረቻ ዘርፍ እ.ኤ.አ በ2025 ከአገሪቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ሃያ በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ዕቅድ ያለው ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ይሄንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ያግዘኛል ብሎ ያስባል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

በአሁኑ ወቅት ዘርፉ በዓመታዊ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻ አምስት በመቶ አይሞላም። ከኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ምርቶችን ወደ ውጭ አገር በመላክ ወደ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል።በአዲሱ የ2011 የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት አዋጁን የማሻሻል ዕቅድ እንዳለ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። ማሻሻያዎቹ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ መንግስታዊ የልማት ተቋማትን ወደ ግል ለማዛወር ከያዘችው ውጥን ጋር የሚያያዙ ሲሆኑ በሌላ በኩል ለባለሃብቶች የሚሰጡ ማትጊያዎች አፈፃፀምን መሠረት ያደረጉ ናቸው።

እየተሻሻለ ባለው የአሰሪና ሠራተኛ ህግ የዝቅተኛ ደሞዝ ወለል ጉዳይ እንደሚካተት የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ ይህ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ከኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ክፍያ ዝቅተኛነት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ቅሬታዎች መፍትሄ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ አክለው ተናግረዋል።