ቦቢ ዋይን፤ "አንዳች የሰውነቴ ክፍል ከስቃይ አልዳነም"

የፎቶው ባለመብት, Bobi Wine
ቦቢ ዋይን
ዩጋንዳዊው ሙዚቀኛና የህዝብ እንደራሴ በእስር ላይ ሳለ ከፍተኛ ስቃይ እንደረሰበትና "አንዳች የሰውነቴ ክፍል ከስቃይ አልዳነም" በማለት በፌስቡክ ገጹ አሳውቋል።
ቦቢ ዋይን በሀገር መክዳት ተከሶ ለእስር ከተዳረገ በኃላ ባለፈው ሳምንት በዋስ መለቀቁ ይታወሳል። አሁን ወደ አሜሪካ አቅንቶ ህክምና እያደረገ ይገኛል።
የኡጋንዳ ወታደራዊ ሀይሎች እስር ቤት ውስጥ እንዳሰቃዩት ከተናገረ ቢቆይም የዩጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ "ሀሰት ነው" ሲሉ አጣጥለውታል።
በሀገር መክዳት የተከሰሰው ቦቢ ዋይን በበኩሉ ክሱን "ግራ የሚያጋባ" ብሎ በሱ በኩል ያለውን እውነታ ይፋ እንደሚያወጣ ተናግሯል።
"በቦት ጫማቸው ረግጠውኛል፣ ደብድበውኛል፣ ከመላ አካለቴ የቀራቸው የለም። አይኔን፣ አፍናጫዬን፣ አፌን፣ ክንዴንና ጉልበቴን ደብድበውኛል። ርህራሄ የሌላቸው ጨካኞች ናቸው" ሲል ቦቢ ዋይን ተናግሯል።
በክፍሉ ሶስት መሳሪያ የተገኘ በማስመሰል ስቃዩን እንዳበረቱበትም ገልጿል። "ብልቴን በሆነ አይነት መሳሪያ መተውኛል። ጉልበቴን በመሳሪያ ሰደፍ ቀጥቅጠውኛል። በስቃይ ሳጣጥር ዝም በል ይሉኝ ነበር" ሲልም ሰቆቃውን ገልጿል።
በህገ ወጥ መንገድ መሳሪያ ይዟል የሚለውን ክስ ወታደራዊው ፍርድ ቤት እንደሰረዘለት ይታወሳል።