የ2010 የጥበብ ክራሞት

የ2010 የጥበብ ክራሞት

2010ን ለመቀበል መስከረም ላይ ሽር ጉዱ የተጀመረው በሙዚቃ ኮንሰርቶች ነበር። የታዋቂ ሙዚቀኞች ፎቶ ከአዲስ ዓመት አብሳሪ አደይ አበባ ጋር ተጣምሮ የሚታይባቸው የኮንሰርት ማስታወቂያዎች እዚህም እዚያም ይታዩ ነበር።

ከመስከረም ጥቅምት፣ ህዳር፣ ታህሳስ . . . እያለ ዓመቱ ሲገፋ ሙዚቃው ብቻ ሳይሆን ፊልሙ፣ ሥነ ጽሑፉ፣ ሥነ ጥበቡም ተሟሙቋል።

ከዓብይ አህመድ እስከ ቴዲ አፍሮ

በዓመቱ አበይት ከነበሩ የሙዚቃ ኮንሰርቶች መካከል የቴዲ አፍሮ "ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር" የተሰኘው ይገኝበታል። "ኢትዮጵያ" የተሰኘው አልበም መለቀቁን ተከትሎ፤ ጥር 12፣ 2010 ዓ. ም. በባህር ዳር ስቴድየም ውስጥ ነበር የተካሄደው።

የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩን የሚያሞጋግሱ ነጠላ ዜማዎች የተለበቁበት ዓመትም ነው። በኦሮምኛ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው የአቡሽ ዘለቀ "አነቃን" የተሰኘው ዘፈን ተጠቃሽ ነው።

አዲስ ሙላት ያወጣው "ሃገሬን" የተሰኘው ነጠላ ዜማ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰኔ 16፣ 2010 ዓ. ም. በመስቀል አደባባይ ያደረጉትን ንግግርን መነሻ በማድረግ ጀምሮ፤ ድምጻዊው የኦሮምያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ለማ መገርሳን ያመሰግናል።

የአብዲ ያሲን "ተደምረናል"፣ የፋሲል ደሞዝ "ሰላም ነው ድግሱ"፣ የሲሳይ ደሞዝ "አማረብሽ ዛሬ" በርካታ አድማጭ ካገኙ ሙዚቃዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, TWITTER

ለዓመታት አልበም ያላወጣችው ማሪቱ ለገሰ "ይገማሸራል" የተሰኘ አልበሟን የለቀቀችው በዚሁ ዓመት ነው። 'የአምባሰሏ ንግስት' የምትባለው ድምጻዊቷ አልበም ሐምሌ 6፣ 2010 ዓ. ም. ተመርቋል።

ዓመቱ የመጀመሪያ አልበማቸውን ለአድማጭ እነሆ ካሉ ድምጻውያን፤ አልበም እስከደጋገሙት ድረስም የተደመጠበት ነው።

የጃኖ ባንድ "ለራስህ ነው"፣ የሮፍናን "ነጸብራቅ"፣ የጃሉድ "ንጉስ"፣ የቤቲ ጂ "ወገግታ"፣ የእሱባለው ይታየው "ትርታዬ" እና የብስራት ሱራፌልን "ቃል በቃል" መጥቀስ ይቻላል።

ዓመቱን ካደመቁ ኮንሰርቶች መካከል መባቻው ላይ የተካሄደው "እንቁጣጣሽ" ይገኝበታል። በካፒታል ሆቴል በተካሄደው ኮንሰርት ሚካኤል ለማ፣ ሳሚ ዳን፣ ዳዊት ጽጌ እና ሌሎችም ድምጻውያን አቀንቅነዋል።

ድምጻውያኑ አልበም ከለቀቁ በኋላ ለአልበም ምርቃት ያዘጋጇቸው ኮንሰርቶችም አድማጮችን የሳቡ ነበሩ። ለአብነት የጃኖ ባንድ "ለራስህ ነው" ኮንሰርት ይገኝበታል።

በሙዚቃ አድማጮች የተወደዱ፣ ሙዚቀኞች የሚሸለሙባቸው "ለዛ"ን የመሰሉ ዓመታዊ የሙዚቃ ውድድሮችም ሳይጠቀሱ አይታለፉም።

ጥቅምት 11፣ 2010 ዓ. ም. በግዮን ሆቴል የተካሄደው "ቢራቢሮ" ኮንሰርት ከባህር ማዶ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኞች መካከል ቶም ስዎንና ኢትዮጵያዊው ሮፍናን የተጣመሩበት ነበር።

አንጋፋው መሀሙድ አህመድና አብዱ ኪያር በአንድ መድረክ ያቀነቀኑበት "ኢትዮጵያዊ ኮንሰርት 2" ሰኔ 23፣ 2010 ዓ. ም. በቃና ስቱድዮ አዳራሽ ተካሂዷል።

ከባለፉት ዓመታት በተለዩ ኮንሰርቶችና ፌስቲቫሎች ከአዲስ አበባ ውጪ የተካሄዱበት ዓመት ነው። በቢሾፍቱ የተከናወነው "ኮረንቲ"ን ጨምሮ በአርባ ምንጭና ሌሎችም ከተሞች ሙዚቃና ፌስቲቫል ቀርቧል።

ባለፈው ዓመት "ጊዜ 1" በሚል የተጀመረው ኮንሰርት "ጊዜ 2" በሚልም ቀጥሏል። "ጊዜ 2" ጥቅምት 18፣ 2010 ዓ. ም. በሚሊንየም አዳራሽ ሲካሄድ፣ ናይጄሪያዊው ዊዝኪድ አንዲሁም አሊ ቢራ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ አብነት አጎናፍር፣ አብርሀም ገብረመድህንና ሌሎችም ድምጻውያን ዘፍነዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ኃይሉ መርጊያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃ ይጫወት በነበረበት ወቅት የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። አሁን በአሜሪካ እየኖረም ቢሆን ግን ሙዚቃ ማቀናበሩን አልተውም።

ባለፉት ዓመታት የባህር ማዶ ሙዚቀኞች በተለይም ዐውደ ዓመት አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ ይጋበዙ ነበር። በዚህ ዓመት ብዙ ሙዚቀኞች ባይመጡም፤ የልደት በአልን (ገና) አስታከው ወደ አዲስ አበባ ብቅ ያሉት የሞርጋን ሄሪቴጅ ወንድማማቾች፤ በኤቪ ክለብ ለልደት በአል ዋዜማ ማቀንቀናቸው ይታወሳል።

"ሚውዚክ ፎር ፒስ" ወይም "ሙዚቃ ለሰላም " በሚል ጥር 16፣ 2010 ዓ. ም. በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ (የፈረንሳይ ባህል ማዕከል) የተካሄደው ኮንሰርት ኢትዮጵያውያኑን ፀደንያ ገብረማርቆስና ሔኖክ መሀሪን ጨምሮ የኬንያ፣ የብሩንዲና የደቡብ ሱዳን ሙዚቀኞችም የተሳተፉበት ነበር።

ዩቲዩብ ላይ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነት ካገኙ የሙዚቃ ቪድዮዎች የወንዲ ማክ "አባ ገዳ" (9.6 ሚሊየን ተመልካች)፣ የሰላማዊት ዩሀንስ "ሀነን" (8.3 ሚሊየን ተመልካች)፣ የያሬድ ነጉ "ዘለላዬ"(7.6 ሚሊየን ተመልካች) ይገኙበታል።

"ሆሄ" እና "ኢትዮጵያ ሆይ"

የሥነ ጽሑፉ ዘርፍ እንዳለፉት ዓመታት በርካታ የወግና የግጥም እንዲሁም ኢ-ልቦለድ መጻሕፍት ለህትመት የበቁበት ነው።

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ተከትሎ የወጡ መጻሕፍት ገበያውን አጨናንቀው ከርመዋል። በሌላ በኩል የሳይንስና የጤና መጻሕፍት በስፋት ተነባቢነት ያገኙበትም ዓመት ነው።

በጤናው ዘርፍ በአእምሮ ዝግመት ዙሪያ የሚያጠነጥነው የዶ/ር ዮናስ ባህረ ጥበብ "አይኔን ተመልከተኝ"፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ "ግርምተ ሳይቴክ" ተነበዋል።

ዓመታዊ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች፤ የመጻሕፍ ሽያጭና ሥነ ጽሑፋዊ ውይይት አስተናግደዋል። በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱም በመድረኮቹ ተመስግነዋል።

የድምፅ መግለጫ,

"ፍቅር እስከ መቃብር"ን በአይፎን 7?''

የክረምት መምጣትን አስመልክተው ከተሰናዱ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች ውስጥ በኤግዚብሽን ማዕከል ከሐምሌ 26 እስከ 30፣ 2010 ዓ. ም. የተከናወነው ንባብ ለሕይወትና የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሰኔ 1 የንባብ ቀንን ተከትሎ ለስምንት ቀናት በአራት ኪሎ ጎዳና ያካሄደው ዐውደ ርዕይ ይጠቀሳሉ።

በርካታ መጻሕፍት አሳታሚዎች፣ አከፋፋዮችና ሻጮች የተገኙበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዐውደ ርዕይ፤ እንዲሁም እንደ እነሆ መጻሕፍት ቤት ባሉ የግል ተቋሞች ተነሳሽነት በየወሩ ማገባደጃ የተከናወኑ ዐውደ ርዕዮችም አይዘነጉም።

ዘንድሮ እንደ "ሰምና ወርቅ" ያሉ አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች የተጠናከሩበት፤ እንደ "ግጥምን በጃዝ" ያሉ የጥበብ መድረኮች ደግሞ ቀጣይነታቸውን ያረጋረጡበት ነበር።

የመጽሐፍ ሻጩ ተስፋዬ አዳልን እድሜ ጠገብ የጽድ መጻሕፍት ቤት ለመታደግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተከናወነው የሥነ ጽሑፍ መሰናዶ ከዓመቱ ክንውኖችም አንዱ ነው።

በእናት ማስታወቂያ እና በጎተ ኢንስቲትዩት (የጀርመን ባሕል ማዕከል) እንዲሁም በሚውዚክ ሜይ ዴይ የሚዘጋጁት ወርሀዊ የሥነ ጽሑፍ ውይይቶች የመጻሕፍት ይዘት የተፈተሸባቸው ናቸው።

ከመስከረም አንስቶ በየወሩ በተካሄዱት መሰናዶዎች ዲስኩር፣ ወግ፣ ተውኔትና ግጥም ቀርቧል። ነቢይ መኮንን፣ ይታገሱ ጌትነት እና አለማየሁ ታደሰ ከተጋባዦቹ መካካል ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, SOLOMON MULUGETA KASSA

በዓመቱ ከወጡ መጻሕፍት የአለማየሁ ገላጋይ "መለያየት ሞት ነው"፣ የክፍሉ ታደሰ "ኢትዮጵያ ሆይ"፣ የቆንጂት ብርሃን "ያላረፉ ነፍሶች"፣ የአበበ ካብትይመር "ንውዘት" እና የሰናይት ፍቃዴ "ማራ" ይጠቀሳሉ።

"ፍቅፋቂ" የተሰኘው የሕይወት እምሻው የወጎችና ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ የታተመውም በዚሁ ዓመት ነበር። የአዳም ረታ "አፍ" መጋቢት 11፣ 2010 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም "የትውልድ አደራ" መጋቢት 7፣ 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ተመርቀው ለንባብ በቅተዋል።

በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጸሐፍት የተሸለሙበት 'ሆሄ' የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ከዓመቱ መርሀ ግብሮች ይጠቀሳል። በወርሀ ሐምሌ የተከናወነው ሽልማቱ በቀጣይ ዓመታትም ይዘልቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ"አብዮት እንደ በረከት" ወደ "ጥበብ በአደባባይ"

ዓመታት ባስቆጠሩ ጋለሪዎች እንዲሁም በቅርቡ ብቅ ብቅ ባሉትም የሥዕልና የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዮች የታዩበት ዓመት ነው። በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምሕርት ቤት የተካሄደው የቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ዓመታዊ ዐውደ ርዕይ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ በወርሀ የካቲት "ሊቶግራፊ፤ ፕሪንቲንግ ዊዝ ስቶን" የተሰኘና በህትመት ጥበብ ላይ ያተኮረ ዐውደ ርዕይ መከናወኑ አይዘነጋም።

ዓመቱ የአንጋፋዎቹ ሠዓሊያን ታደሰ መስፍን "ፒላርስ ኦፍ ላይፍ፤ ዘ ፓወር ኤንድ ግሬስ ኦፍ ማርኬት ላይፍ"፣ የጥበበ ተርፋ "ኢንዱሪንግ ስፒሪት" እና የበቀለ መኮንን (ተባባሪ ፕሮፌሰር) "ባሩድና ብርጉድ" ዐውደ ርዕዮች የታዩበት ነበር።

ዓመቱ የነቢላ አብዱልመሊክ "አፍሮ ትሮተር ዳየሪስ አዲስ- ካርቱም - ማዳጋስካር" የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ እና የስናፍቅሽ ዘለቀ "ራስን ፍለጋ" የሥዕል ዐውደ ርዕይ የተስተናገደበትም ነበር።

በፈረንሳይ ባህል ማዕከል ለዕይታ ከበቁ ዐውደ ርዕዮች መካከል ከግንቦት 13 እስከ ሰኔ 2፣ 2010 ዓ. ም. የዘለቀው የለይኩን ናሁሰናይ "ነጭ መስመር" አንዱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, TWITTER

በቅርቡ በተከፈተው ፈንድቃ ጋለሪ የሮቤል ተመስገን "ተንሳፋፊ ጀበናዎች" ዐውደ ርዕይ ታይቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨረ የመጣው የግል ጋለሪዎች ለሥነ ጥበቡ ቦታ በመስጠት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ማሳያም ይሆናል።

ሠዓሊ ቸርነት ወልደገብርኤል በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ለአንድ ወር እየሰራ እንዲኖር (በእንግሊዘኛ ሬዚደንሲ) ተሰጥቶት ነበር። ሲጠናቀቅም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያተኮረ "አብዮት እንደ በረከት" የተሰኘ ዐውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ነበር። ከህዳር 22፣ 2010 ዓ. ም. ጀምሮም በአካዳሚው ታይቷል።

በዘመናዊ የሥነ ጥበባት ሙዝየም የገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል፤ የሥነ ጥበብ ዐውደ ርዕዮች ብቻ ሳይሆን ውይቶቶችም ተካሂደዋል። የጥበብ አፍቃሪዎች ከሙያተኞች ጋር የተገናኙባቸው መድረኮች ነበሩ።

በማዕከሉ ከተካሄዱ ውይይቶች ግንቦት 14፣ 2010 ዓ. ም. የተካሄደው "ምን ነበረ?" ይጠቀሳል። ኤልሳቤጥ ወልደጊዎርጊስ (ዶ/ር)፣ ሮቤል ተመስገን እና ሔኖክ መልካምዘር አወያዮች ነበሩ። ሔኖክ መልካምዘር ከመጋቢት 1፣ 2010 ዓ. ም. ጀምሮ በጠልሰም ላይ ያተኮረውን "ጠልሰማዊ ጥበብ" ዐውደ ርዕይም አቅርቧል።

"ጥበብ በአደባባይ" የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው መርሀ ግብር ሙዚቃና ሥነ ጥበብ የተጣመሩበት ነበር። ሀሳቡ የጥበብን ስራዎችን ከጋለሪ አውጥቶ ማህበረሰቡ ባለበት ማድረስ ነው። የጎዳና ላይ ጥበብ ብዙም ባልተለመደበት ኢትዮጵያ መካሄዱ የሚበረታታ ጅማሮ ነው።

"ጥበብ በአደባባይ" የተጀመረው ሚያዝያ 27 ሲሆን እስከ ግንቦት 19፣ 2010 ዓ. ም. በስድስት ኪሎ፣ በመገናኛ፣ በቦሌ መድሀኔአለም፣ በመስቀል አደባባይና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ጠቢባን እየተዘዋወሩ ለማህበረሰቡ ስራቸውን አሳይዋል።

አዲስ የቪድዮ ስነ ጥበብ ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ብዙም እውቅና ያላገኘውን የቪድዮ ስነ ጥበብ ለማሳወቅ ከጋለሪዎች እስከ ጎዳናና ጠጅ ቤት ድረስም ዘልቋል።

በኢትዮጵያውያንና በሌሎችም ሀገሮች የቪድዮ ስነ ጥበብ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ቪድዮዎች በፈንድቃ ጋለሪ፣ በአዲስ አበባ ሙዚየም፣ በብሔራዊ ቴአትር ጋለሪና በጅማ ጠጅ ቤት ታይተዋል።

"ኮንቴምፕረሪ ናይትስ" በሚል ዘንድሮ የተጀመረው ወርሀዊ መሰናዶ፤ ዘመናዊ ሥነ ጥበብን ያማከለ ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥ በአዲስ ፋይን አርት ጋለሪና በፈረንሳይ ባህል ማዕከል ተካሂዷል።

ወጣት የዲጂታል ሥነ ጥበብ ሙያተኞች ተሰባስበው ስራዎቻቸውን ያሳዩበት "የሃ" የዲጂታል ሥነ ጥበብ ዐውደ ርዕይ ዓመቱ በአዳዲስ የጥበብ ክንውኖች እንዲታወስ ካደረጉ አንዱ ነው።

በሸራተን አዲስ በየዓመቱ የሚካሄደው "የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ" የተሰኘው ዐውደ ርዕይ 10ኛ ዓመቱን ያከበረው በዚሁ ዓመት ነው። ከህዳር 26 እስከ 30፣ 2010 ዓ. ም. በተካሄደው ዐውደ ርዕይ 60 ጠቢባን ስራዎቻቸውን አሳይተዋል።

የሥነ ጥበብ ውጤቶች የሚሸጡበት ዓመታዊው "ዘ ቢግ አርት ሴል" ዘንድሮም ቀጥሎ ከ1,000 በላይ ስራዎች ለገበያ ቀርበዋል።

"አንቺ ሆዬ" እንዲሁም "እርቅ ይሁን"

በ2010 ዓ. ም. ወደ 70 ፊልሞች ወጥተዋል። ቁጥሩ ካለፉት ዓመታት አንጻር አነስተኛ የሚባል ነው። በሌላ በኩል መርካቶ አካባቢ አዲስ ሲኒማ ቤትም መከፈቱ ይጠቀሳል። የግል ሲኒማ ቤቶች በተለያዩ አካባቢዎች መከፈታቸው ከፊልም በተጨማሪ አዳዲስ የፊልም ፌስቲቫሎች ተደራሽነታቸው እንዲሰፋ አግዟል።

እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው በሐምሌ ወር ቫድማስ ሲኒማ ቤት "ብላክ ብራዚሊያን ፊልም" የተሰኘ የሁለት ቀን መሰናዶ መዘጋጀቱ ነው። "ስፒሪት ኢን ዘ አይ"፣ "ካሮሊና" እና ሌሎችም ፊልሞች ታይተዋል።

በዛው ሲኒማ ቤት "አዲስ ፎቶ ኤንድ ፊልም ፌስት" የተሰኘ የፎቶግራፍና ፊልም ፌስቲቫል ተካሂዷል። ፊልሞች ታይተዋል። ውይይትም ተደርጓል።

ግንቦት ውስጥ የተካሄደው "አንቺ ሆዬ" የፌሚኒስት ፊልም ፌስቲቫል ሴታዊትና የሎ ሙቭመንት በጥምረት ያዘጋጁት ሲሆን፣ ለሶስት ቀናት የተምሳሌት ሴቶችን ህይወት የሚያስቃኙ ፊልሞች ታይተዋል። በስንዱ ገብሩና አስናቀች ወርቁ ህይወት ላይ ያተኮሩን ፊልሞች ታይተዋል።

በዘጋቢ ፊልሞች ላይ ያተኮረው ዓመታዊው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ከኢትዮጵያና ከተቀረው አለም የተውጣጡ ዘጋቢ ፊልሞች በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ በጣልያን ባህል ማዕከልና በሀገር ፍቅር ቴአትር የታዩበት ነበር። ከፊልም ሰሪዎች ጋርም ውይይት ተደርጓል።

"እርቅ ይሁን" በዓመቱ ውስጥ ለተመልካቾች ከቀረቡ ፊልሞች አንዱ ነው። "ለፍቅር ስል"፣ "አላበድኩም"፣ "ሚስቴን ዳርኳት"፣ "ወደ ኃላ"፣ "እንደ ባልና ሚስት"፣ "አብሳላት"፣ "ባንተ መንገድ" እና "ዘናጭ" በዓመቱ ከወጡ ፊልሞች መካከል ይጠቀሳሉ።

ለፊልም ሰሪዎች እውቅና ከሚሰጡ የሽልማት መሰናዶዎች አንዱ "ጉማ" አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል "ሰንኮፋ፤ ዘ አርት ኦፍ ስቶሪ ቴሊንግ" በሚል አርዕስት ተካሂዷል።

በታሪክ ነገራ ላይ ያተኮረው ፌስቲቫሉ በፊልም ሰሪዎች መካከል ውይይት በማድረግና ባለፈው ዓመት ከወጡ ፊልሞች የተመረጡትን በመሸለም ተጠናቋል።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥና የውጪ ፊልሞች በቫድማስ ሲኒማ፣ በፈረንሳይ ባህል ማዕከልና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ታይተዋል።

የድምፅ መግለጫ,

በማንተጋፍቶት ስለሺ ተፅፎ የተሰናዳው ግርታ ፊልም በቅርቡ በቤልጂየም በተዘጋጀ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ አሸናፊ ሆኗል።

በዋነኛነት የፈረንሳይ፣ የጣልያንና የጀርመን ባህል ማዕከሎች የተለያዩ ሀገራት ፊልሞችን በማምጣት ያሳዩበትም ዓመት ነው። ዓመታዊው የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል እንዳለ ሆኖ፤ ሌሎችም የምዕራቡና የምስራቁ አለም ፊልሞች የታዩባቸው ፌስቲቫሎች ተከናውነዋል።

ዓመቱ ሲጠቃለል. . .

በዓመቱ ውስጥ ከተከናወኑ የጥበብ መሰናዶዎች በተጨማሪ ማህበራዊ ጉዳዮችን በጥበብ የዳሰሱም ይገኙበታል። ሜላት የተባለች የኩላሊት ህመም የገጠማት ወጣትን ለመታደግ መጋቢት 20፣ 2010 ዓ. ም. "ለሜላት እኔም አለሁላት" የተባለ ኮንሰርት ተካሂዶ ነበር። ከኮንሰርቱ የተገኘውን ገቢ ለህክምና ወጪ እንድታውለው ያለመ ነበር።

መጋቢት ወር ላይ ከኢትዮጵያና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ የሰርከስ ሙያተኞች የሰርከስ ትርኢት ያሳዩበት "አፍሪካን ሰርከስ አርትስ ፌስቲቫል" በመኮንኖች ክበብ ተካሂዷል። የህጻናት መዝናኛ እንዲሁም ምግብና መጠጥም ቀርቦ ነበር።

"ዲዛይን ዊክ አዲስ" የሥነ ህንጻ ዲዛይን፣ የልብስ ዲዛይን፣ ምግብ፣ መጠጥና መዋቢያ ምርቶችም የቀረቡበት ነበር። በተያያዥ በፋሽን ዘርፍ ተጠቃሽ ከሆኑ ትርኢቶች መካከል "ዘ ባግ ሾው"፣ "ሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ዊክ" እና "አፍሪካን ሞዛይክ" ይገኙበታል።

ታላቁ ሩጫን በማስመልከት የተሰናዳው "ግሬት ኢትዮጵያን ኮንሰርት" ህዳር ወር ላይ ተካሂዷል። ከኢትዮጵያ ንዋይ ደበበና ማዲንጎ አፈወርቅ ከውጪ ሀገር ሉችያኖ፣ ካሊ ፒ እና ቲዎኒ በግዮን ሆቴል ያቀነቀኑበት ነበር።

ወቅት ተኮር ከሆኑ ሁነቶች በዓመቱ መግቢያ ላይ የነበረውና ብርዳማውን ጥቅምት ያማከለው "በጥቅምት አንድ አጥንት" የስጋና ቢራ ፌስቲቫል ተጠቃሽ ነው። በዓመቱ ማገባደጃ ደግሞ የትምህርት መጀመርን ያስታከከው "አንድ እሽግ ለአንድ ልጅ" ተካሂዷል።

የትምህርት መሳሪያ ለማሟላት አቅማቸው ያልፈቀደላቸው ታዳጊዎችን መርዳት ላይ ያተኮረ ነበር።