'መቐለ' በምፅዋ

የፎቶው ባለመብት, Horn Affairs
ዛሬ (ረቡዕ) ጠዋት በምፅዋ የሆነው ነገር ተራ "የመርከብ ጭነት ንግድ" ሊባል የሚችል አይደለም። ለዚህ አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ታሪካዊም፣ ፖለቲካዊም፣ ሰዋዊም ምክንያቶችን አሉ።
ተኳርፈው በቆዩ ወንድማማች አገራት መካከል መሆኑና ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መደረጉ ቀዳሚው ምክንያት ነው፤ ለአንዳንዶች ደግሞ የተጀመረው የሰላም ስምምነት 'መልህቁን እየጣለ' ስለመሆኑ እንደ አንድ ማሳያ ይጠቅሱታል።
"አቀባበሉም ቢሆን ደማቅና ቤተሰባዊ ነበር" ያሉን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ የመርከቧ ምፅዋ መገኘት በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በኤርትራም በኩል ልዩ ስሜትን መፍጠሩን አልሸሸጉም።
አቶ ሮባ ይህን እንዲሉ ያስቻላቸው በወደቡ የተመለከቱት ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም። መርከቧ መልህቋን ስትጥል በድምቀት የተቀበሏት "ምናልባት በአንድ ወቅት የድርጅታችን ባሕረኛ የነበሩ፤ አሁን ግን የወደቡ ሠራተኞች የሆኑ ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኤርትራ በኩል ያሉ ሠራተኞች ጭነቱ ከመጀመሩ በፊት ሲጠያየቁ የነበሩት ዘመድ አዝማዶቻቸውን፣ ድሮ አብረው ይሠሩ የነበሩ ባልደረቦቻቸውን ነበር። "ይህ በራሱ ትልቅ ሐብት ነው" የሚሉት አቶ ሮባ የሁለቱ አገር መሪዎች መርከቧ ላይ በመውጣት የጭነት ንግዱን ታሪካዊነት አጉልተውታል ይላሉ።
ይህ ኩነት መታሰቢያነቱ ለሰላሙ መሳካት ጉልህ ሚና ለተጫወቱት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እንዲሆን ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ባንዲራ ጎን የዐብይ ስም በ"ኢንተርናሸናል ማሪታይም ሲግናል ኮድ" እንዲለጠፍ ተደርጓል።
የፎቶው ባለመብት, የማነ ገብረመስቀል
"ምፅዋ ምርጥ ወደብ ናት"
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት የጭነት ንግድ ላይ በስፋት ይታወቃል። በመደበኛነት የአገሪቱን ወጪና ገቢ ሸቀጦችን ከማመላለስ ባሻገር ለሌሎች አገሮችና ኩባንያዎች የኮንትራት (ቻርተርድ) የጭነት ሥራን ይሠራል።
የዕቃ ማጓጓዣ አገልግሎትንም በውጭ አገር ወደቦች መካከል ያቀርባል። አህጉር አቋራጭ (ክሮስ ትሬድ) የቻርተር አገልግሎትንም እንዲሁ። ይህን ሥራ የሚያቀላጥፈው ታዲያ በኮሚሽን ወኪሎቹ አማካኝነት ነው።
የምፅዋን ጭነት እንዲያጓጉዝ የኢትዮጵያ መርከብ የተመረጠው ጨረታ በማሸነፉ እንደሆነ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው ጠቆም አድርገዋል።
ዛሬ ጠዋት ምጽዋ የደረሰችው "መቐለ" መርከብ ጉዞዋ የሚሆነው ወደ ቻይና ነው። እግረ መንገዷንም የሳዑዲን ማዕድን ጭናለችም ተብሏል። ከኤርትራ የጫነችው 11ሺህ ሜትሪክ ቶን ዚንክ እንደሆነም አቶ የማነ አረጋግጠዋል።
ከእንዲህ ዓይነቱ የአንድ ጊዜ የኮንትራት ሥራ ወጥቶ ወደፊት በመደበኛነት ይህንን ሥራ ለመጀመር በሁለቱ አገራት መካከል ድርድር እየተካሄደ እንደሆነ ለቢቢሲ የጠቆሙት አቶ ሮባ ሂደቱ ከተሳካ በወር እስከ ስምንት መቶ ሺ ዶላር የውጭ ምንዛሬን ለድርጅታቸው እንደሚያስገባ ይገምታሉ።
"ከኤርትራ ወንድሞቻችን በኩል ጥያቄዎች እየቀረቡልን ነው። የእነሱን ገቢ ጭነት በእኛ መርከብ ለማጓጓዝ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ግን እነዚህንና አጠቃላይ የትራንዚት ኮሪደር አጠቃቀሞችን በተመለከተ ስምምነቶች ለማካሄድ በድርድር ላይ ነን" ብለዋል፤ ለቢቢሲ።
ሆኖም ለእርሳቸው የዛሬው የምፅዋ ኩነት ከንግድ ሽርክናው ባሻገር የሕዝብ ሕዝብ ትስስሩ አንዱ ማስፈጸሚያ ስልት ሆኖ ነው የሚታያቸው።
ያም ሆኖ ምፅዋ አስተማማኝ ወደብ እንደሆነች፣ በዘመናዊ ማሸነሪዎች መታገዟ፣ ሌሎች ወደቦች ላይ ሦስት ቀናትን የሚወስድ ሥራ ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ እንደሚያጠናቀቅም ተናግረዋል።
"በቂ ፋሲሊቲ አላቸው። የሥራ ባሕሉም አለ። በአጠቃላይ ምፅዋ ምርጥ ወደብ ናት" ሲሉ አረጋግጠዋል፤ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ።
የጅቡቲ ነገር
በዚህ ሂደት የጅቡቲ ሚና ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሮባ፤ የወደብ አገልግሎት ከአዋጪነትና ከቅርበት አንጻር እንደሚለካ ካብራሩ በኋላ ሁልጊዜ አማራጭ ይዞ መገኘት፣ ተጨማሪ አቅም ይዞ መሄድ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ሂደቱም የተቀመጠ ነው ይላሉ።
ይህንን ሂደት ጂቡቲዎችም በይሁንታ የሚቀበሉት እንደሆነም ያብራራሉ። "በጂቡቲ ወደብ ብዙ ኢንቨስት አድርገናል፤ በጋራ። ጥሩ ወደቦች አሏቸው፤ እየተጠቀምንበትም ነው። ተጨማሪ ደግሞ የወንድሞቻችንን የኤርትራን ወደቦች እንጠቀማለን" ይላሉ።
ምናልባት ኢትዮጵያ ፊቷን ጠቅልላ ወደ ኤርትራ ታዞር እንደሆኑ ሲጠየቁ "እነ ጀርመን እኮ የባሕር በር እያላቸው፤ የሌላ አገር ወደብ ይጠቀማሉ። የወደብ አጠቃቀም ስትራቴጂ ሲታቀድ ርቀትና አዋጪነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ሌላ ወደብ መጠቀም አሉታዊ አይደለም። ኢትዮጵያ ሌሎች ተጨማሪ ወደቦች ያስፈልጓታል" ሲሉ በአራቱም አቅጣጫ ያሉ ክልሎችን በመዘርዘር ያስረዳሉ።
"እያወራን ያለነው የንግድ የኢኮኖሚ ማሳለጫ መንገድ ስለሆነው ወደብ ነው፤ የባህር በር ሌላ ጉዳይ ነው።"