ኬንያ ቻይናዊውን በዘረኛ ንግግሩ ምክንያት ልታባርር ነው

ቻይናዊ ሊዩ ጂያኪ

የፎቶው ባለመብት, Immigration Kenya twitter

የኬንያዊያንን የሚያንቋሽሽ ቃላትን ሲጠቀም በቪዲዮ የተቀረፀው ቻይናዊ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ገለፁ።

መስሪያ ቤቱ ጨምሮ እንዳሳወቀው የግለሰቡ የሥራ ፈቃድ የተሰረዘ ሲሆን ከኬንያ እንደሚባረርም አመልክተዋል።

ሊዩ ጂያኪ የተባለው ቻይናዊ "ሁሉም ኬንያዊያን ፕሬዝዳንቱን ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ ዝንጀሮዎች ናቸው" ሲል የሚያሳይ ቪዲዮ በስፋት ከተሰራጨ በኋላ በኬንያዊያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

የኬንያ ፖሊስም ቪዲዮው በርካታ ሰዎች እጅ ከገባ ከሰዓታት በኋላ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎታል።

በሞተር ሳይክል ንግድ ላይ የተሰማራው ቻይናዊ ይህንን ለማለት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም ንግግሩ የተቀረፀው ከሥራ ሊያባርረው ከነበረ ሰራተኛ ጋር በነበረው ምልልስ ወቅት ነበር።

ሰራተኛውም በጊዜው ለቻይናዊው ግለሰብ "የምታደርገው ነገር ስህተት ነው" እያለ ሲሞግተውና እሱም "ግድ አይሰጠኝም" በማለት ሲመልስለት በቪዲዮው ላይ ይታያል።

ቻይናዊው ጨምሮም ጥቁሮችን የሚያንቋሽሽና ከዝንጀሮ ጋር የሚያመሳስሉ ነገሮችን በማንሳት ከእነሱ ጋርም መነጋገር እንደማይፈልግ የመጣውም ገንዘብ ፍለጋ መሆኑን ከሰራተኛው ጋር ሲመላለስ ይሰማል።

ይህንን ንግግር በተመለከተ እራሱም ሆነ በሚወክለው የሕግ ባለሙያ በኩል ምንም አይነት አስተያየት አልተሰጠም።

ከሦስት ዓመታት በፊት ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ የቻይናዊያን ምግብ ቤት ከአመሻሽ 11 ሠዓት ጀምሮ አፍሪካዊያንን አናስተናግድም የሚል አሰራር እንደነበር ይፋ ወጥቶ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የኬኒያ መንግሥት ምግብ ቤቱን ለአጭር ጊዜ ዘግቶ ባለቤቱን በማሰር ክስ መስርቶበት እንደነበር ይታወሳል።