አል-በሽር ካቢኔያቸውን በተኑ

አልበሽር

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አል-በሽር ሃገሪቱ የገጠማትን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ለመቀልበስ በማሰብ ካቢኔያቸውን በተኑ።

በዚህም መሰረት 31 የነበሩት የመንግሥት ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ወደ 21 ዝቅ ይደረጋሉ።

ፕሬዚዳንት አልበሽር ሱዳን የገባችበትን ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ለማስወገድ የወሰድኩት እርምጃ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ መንግሥት ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ በማቆሙ የዳቦ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ነበር።

የሱዳን የመገበያያ ገንዘብም ዋጋ እንዲቀንስ በመደረጉ ከውጪ ሃገራት ስንዴ እና ሌሎች ምርቶችን በቀላሉ መግዛት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ከ7 ዓመታት በፊት ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ከተለየች በኋላ የሱዳን ምጣኔ ሃብት ችግር ላይ ወድቋል።

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ስትለይ 75 በመቶ የሚሆነውን የነዳጅ ሃብት ይዛ ነበር ነጻነቷን ያወጀችው።

የ74 ዓመቱ አልበሽር ሱዳንን ላለፉት 25 ሲመሩ ቆይተዋል።