የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የቅዳሜና እሁድ ውጤቶች

ጌታነህ ከበደ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በፈረንጆቹ 2019 ካሜሮን ላይ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለመላፍ ሃገራት የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን እያካሄዱ ይገኛሉ። የቅዳሜ እና አሁድ ጨዋታዎች ውጤት ምን እንደሚመስል እንቃኝ።

ሃዋሳ ስታደየም ላይ ከሴራሊዮን አጋዋ ጋር ግጥሚያዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ ጌታነህ ከበደ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1 - 0 በማሸነፍ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቧን መያዝ ችላለች።

በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ጋና እና ኬንያ ያደረጉት ግጥሚያ ደግሞ በኬንያ 1 - 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዚህም በምድቡ ውስጥ የሚገኙት አራቱም ሃገራት በእኩል 3 ነጥብ ላይ ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, CAF

ኢትዮጵያ ቀጣይ ጨዋታዋን ከኬንያ ጋር በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም መስከረም 30/2011 ላይ እንደምታደርግ ይጠበቃል።

ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ ጨዋታዎች ኮሞሮስ ከካሜሮን እና ጋቦመን ከብሩንዲ 1 አቻ፤ ደቡብ አፍሪቃ 0 - 0 ሊቢያ፤ በተመሳሳይ ኡጋንዳ ከታንዛንያ 0 - 0 ተለያይተዋል።

በሌሎች ጨዋታዎች ኢኳቶሪያል ጊኒ ሱዳንን 1 - 0፤ ናይጄሪያ ሲሼልስን 3 - 0፤ ጋምቢያ ከአልጄሪያ እና ናሚቢያ ከዛምቢያ 1 አቻ፤ ሞዛምቢክ ከጊኒ ቢሳው 2 አቻ፤ ሞሪታንያ ቡርኪና ፋሶን 2 - 0፤ ግብፅ ኒጀርን 6 - 0፤ እንዲሁም መሮኮ ማላዊን 3 - 0 መርታት ችለዋል።

እሁድ ዕለት በተደረጉ ጨዋታዎቸች ደግሞ ማዳጋስካር እና ሴኔጋል 2 አቻ ሲለያዩ ሌሴቶ ኬፕ ቨርድ፤ ኮንጎ ከዚምባብዌ እንዲሁም ላይቤሪያ ከ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአንድ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ቱኒዚያ ስዋዚላንድን በገዛ ሜዳዋ 2 - 0፤ ኮትዲቯር ሩዋንዳን 2 - 1፤ ማሊ ደቡብ ሱዳንን 3 - 0፤ ጊኒ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክን 1 - 0 ረተዋል፤ ቶጎ ከቤኒን ያደረጉት ፍልሚያ ደግሞ ያለግብ ተጠናቋል።