ሥራ ፈጣሪው የጋናን የወደፊት የፈጠራ ሰዎች ትውልድ እየፈጠረ ነው

ለትንሻ ቦርሳ ምስጋና ይግባትና በመላው ጋና የሚገኙ ልጆች የሳይንስ ህልማቸውን መቀጠል ችለዋል
አጭር የምስል መግለጫ ለትንሻ ቦርሳ ምስጋና ይግባትና በመላው ጋና የሚገኙ ልጆች የሳይንስ ህልማቸውን መቀጠል ችለዋል

"እኔ... እኔ... እኔ ..." ከ30 የሚበልጡ ልጆች በአረንጓዴ ሸለቆ ጥግ ከሚገኘው ክፍላቸው ትናንሽ የእንጨት ወንበሮቻቸው እየዘለሉ በደስታ ይጮሃሉ።

ውድድሩ ከጋና ዋና ከተማ አክራ ወጣ ብሎ በሚገኘው በረኩሶ መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሆን ውድድሩም ሽቦዎችን እና ትራንዚስተሮችን በማገናኘት ማን ትንሽዬ የቃጭል ድምጽ የምታሰማ መሳሪያ እንደሚሰራ ማየት ነው፡፡

በሰከንዶች ውስጥ ክፍሉ በብዙ ባለከፍተኛ የቃጭል መሰል ድምጾች ተሞላ። ልጆቹ በደስታ አበዱ። ማን እንዳሸነፈ ለመናገር አልተቻለም።

አዲሱ የማዋለጃ ቦርሳ የእናቶችን ህይወት እየታደገ ነው

የምግብ ብክነትን ለማስወገድ አዲስ ፈጠራ

የዛሬ ዓመት እነዚህ ታዳጊዎች ኤሌክትሮኒክስን እየተማሩ የነበሩት በጥቁር ሰሌዳ፣ በጠመኔ እና በጥቂት መጽሃፍት ነበር። አሁን መንገዳቸውን ለማቃናት የሚፈልጓቸው ነገሮች ሁሉ ከፊት ለፊታቸው አሉላቸው።

የመማሪያ መጽሃፍት ፈጠራ

የ25 ዓመቱ ቻርለስ ኦፎሪ አንቲፐም ከዚህ ሁሉ ጀርባ አለ።

የመማሪያ መጽሃፍ ዋጋ (15 ዶላር) እና መጠን ያላት በኤሌክትሪክ መሳሪያዎች የተሞላች ትንሽ ጥቁር ሳጥን እውን አደረገ።

"ቦርሳዎችን በተማሪዎች ወንበር ላይ በማስቀመጥ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ መስመር ሲገነቡ በተማሪዎቹ አይን ላይ የሚፈነጥቀውን ብርሃን ማየት መቻል፤ ያ ነው እርምጃችንን እንድንቀጥል የሚረዳን" ይላል።

ቻርለስ፤ ዴክስት ቴክኖሎጂ የተሰኘውን ኩባንያውን የመሰረተው ከ18 ወራት በፊት ነው። አሁን ዘጠኝ ሰራተኞች አሉት እስካሁንም ከ5 ሺህ በላይ ቦርሳዎችን በመላው ጋና ለሚገኙ የመንግሥት እና የግል ት/ቤቶች ሽጧል።

ሀሳቡን የጠነሰሰው አንድ ቤት ከሚጋራው ሚካኤል አሳንቴ አፍሪፋ ጋር በዩኒቨርስቲ የመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ነው። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ጋና ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ልጅ አንድ ቦርሳ እንዲኖረው ይፈልጋሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ቻርለስ ኦፎሪ አንቲፐም የሳይንስ ቦርሳውን በመላው አፍሪካ ለሚገኙ ልጆች የማጋራት ህልም አለው

"መጽሃፍ ውስጥ ያለን እውቀት መቅሰም አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ዋናው ጠቃሚ ነገር በሙከራ መለማመድ መቻል ነው" ይላል።

ከ2020 ጀምሮ ያሉት አስርት ዓመታት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና ሒሳብ የመሳሰሉትን መስፈርቶች ወደሚጠይቁ ሥራዎች እንደገና የሚዋቀሩባቸው ዓመታት እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ምን ያህሎቹ የዓለማችን ሥዎራች እነዚህን አዳዲስ ክህሎቶች ወደሚጠይቁ መስፈርቶች እንደሚሸጋገሩ በትክክል ማንም አያውቅም። ወደ 80 በመቶው አካባቢ እንደሚሆኑ ግን ግምቶች ተቀምጠዋል።

ነገር ግን ከሰሃራ በታች ባለው ክልል ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስናና ሒሳብ ትምህርት እና ስልጠና ላይ የሚያፈሱት መዋዕለ ነዋይ በእጅጉ ወደኋላ የቀረ ነው። የተባበሩት መንግሥታት እንደሚገልጸው አንድ እራሱን የቻለ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ማዳረስ እና ንጽህና ማሻሻልን የተመለከተውን የዘላቂ ልማት ግብ ለማሳካት ብቻ በርካታ መሃንዲሶችን ይፈልጋል።

የጋና ሳይንስ ማህበር አባል የሆኑት ዶክትር ቶማስ ታጎኢ እንደሚሉት ሀገሪቱ በቂ መሃንዲሶች እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስለሌሏት በልጆች ላይ የሳይንስ ፍቅር እንዲያድረባቸው ይህ ፈጠራ በራሱ ጠቃሚ ነው።

"ይህ የዲጅታል ዘመን ነው። እናም ይህንን አጋጣሚ ሊጠቀሙበት የሚችሉ ሰዎችን እንፈልጋለን" ይላሉ። "በዚህም ከታዳጊ ሃገሮች ወጥተን በሳይንስ ሙያተኞች የምንታወቅ ልንሆን እንችላለን።"

ሳይንስ መሪነት

ቻርለስ ያደገው ሳይንስ ትልቅ ቦታን በያዘበት ቤት ውስጥ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ህይወታቸው ያለፈው አባቱ በአካባቢው በሚገኝ ት/ቤት ሳይንስ ያስተምሩ ነበር።

"ሁሌጊዜም ማንኛውንም ያገኘነውን እውቀት እንድንቀስም ይፈልግ ነበር። በተለይ ከሳይንስ ጋር የተገናኙ ነገሮች።"

ነገር ግን ቻርለስ ት/ቤት እያለ በይነ-መረብም ሆነ መሰረታዊ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቁሳቁስ ማግኘት አይችልም ነበር። የገደቡኝ በእጄ ላይ የነበሩት መገልገያዎች ናቸው። ይላል ለዛሬዎቹ ተማሪ ልጆች ይህንን መቀየር እንደሚፈልግ በማከል።

"ሥራዬ በቻልኩት አቅም እኔ በአባቴም ከተደረገልኝ በላይ ቀጣዩን ትውልድ አቅም ማጠናከር መሆን እንዳለበት ይሰማኛል። ይህም ከፊት የሚጠብቋቸውን ፈተናዎች መወጣት እንዲችሉ ይረዳቸዋል።"

አጭር የምስል መግለጫ የሳይንስ ቦርሳው የሚጠይቀው ወጪ 15 ዶላር ብቻ ነው፡፡

ከሰሜን ምዕራብ ቤሬኩሶ የስድስት ሠዓት መንገድ ርቀት ላይ በኩማሲ ከተማ በሚገኝ የቴክኖሎጂ ማዕከል ውስጥ ባለች ትንሽ ሰርቶ ማሳያ የቻርለስ ቡድን የሳይንስ ቦርሳዎችን በማሰናዳት ሥራ ተጠምዷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ቀጫጭን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦዎችን በትናንሽ መቆጣጠሪያ ወይም ርዚስተሮች ላይ እየበየዱ ነው።

"እሺ ይሄ ነው" አለ ቻርለስ በኩራት ትንሿን ጥቁር ሳጥን ይዞ።

የአጠቃቀም መመሪያውን፣ የኤሌክትሮኒክ ክፍሎችን፣ የኤሌክትሮ ማግኔት የብረት ቁርጥራጮችን፣ የብርሃን ሳጥኑን፣ መስታውቶችን በመሃል ደግሞ ሁሉንም የሚያንቀሳቅሱትን ባትሪዎች አንድ በአንድ ያሳያል።

ቻርለስ የሳይንስ ቦርሳዎችን ከጎረቤት አይቮሪኮስት ካካዋ አምራች ማህበረሰቦች ውስጥ ላሉ ት/ቤቶች ሊያስተዋውቅለት ከሚችል ደንበኛ ጋር የስልክ ቀጠሮ አለው፡፡

ጥልቅ ሙያዊ ፍቅር ያለው የሽያጭ ሰራተኛ ነው፤ ሁሉንም ጥያቄዎች ዘና ብሎ ይመልሳል። ስልኩን እንደጨረሰ ፈገግታ ፊቱን ሞላው። "ጥሩ ነበር" አለ ለሙከራ የተወሰኑ ቦርሳዎችን ለመግዛት መስማማታቸውን በማብራራት።

"ይህ ተጨማሪ የሥራ ትዕዛዝ ወይም በሳይንስ ቦርሳው ላይ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲገኝ ሊያደርግ ይችላል" ይላል።

ወደ ቤሬኩሶ ስንመለስ ከት/ቤቱ ትንሽ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ባለው አቧራማ መንገድ አቅራቢያ የ15 ዓመቷ ፕሪንሰስ ማካፉይ ከት/ቤት ጓደኞቿ ጋር ተቀምጣ የቤት ሥራዋን ትሰራለች።

ቤተሰቦቿ የሚኖሩት ጨርሶ ባላለቀ ቤት ውስጥ ነው። ኤሌክትሪክ ይቅርና አንድም ግድግዳ የለውም። ፀሐይ ስለጠለቀች ራሳቸው የፈጠሯትን አንዲት መብራት ከጠረጴዛው መሃል አስቀምጠው ነው የሚሰሩ።

አጭር የምስል መግለጫ ፕሪንሰስ ማካፉይ እና የክፍሏ ልጆች የሳይንስ ቦርሳውን በመጠቀም ውድድር አሸንፈዋል

"አራት ማዕዘን መብራት ነው" ትላለች ፐሪንሰስ በኩራት። "ይህም ማለት ሁላችንም የቤት ሥራችንን ለማየት አንደኛውን ጎን መጠቀም እንችላለን ማለት ነው።" ፕሪንሰስና 12 ሴት ጓደኞቿ በዚህ ፈጠራቸው በአካባቢያቸው የተካሄደውን የሳይንስ ውድድር አሸንፈዋል። ለዚህም የሳይንስ ቦርሳውን ተጠቅመዋል።

"ከሳይንስ ቦርሳዎቹ በፊት የሳይንስ ክፍለ ጊዜያችን አሰልቺ ነበር። ሁሉም ነገር ንድፈ- ሃሳብ ስለነበር እየተረዳነው አልነበረም" ትላለች።

ለቻርለስ አዲስ የፈጠራ ሰዎች ትውልድ እውን የማድረግ ሀሳብ ማለት ተስፋ ሊያደርገው የሚችለው ነገር በሙሉ ማለት ነው።

"የሳይንስ ቦርሳቸውን ተጠቅመው ተማሪዎች በአዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ብቅ ሲሉ ማየት በእርግጥም እውን ለማድረግ ስንሞክረው የቆየነው ጉዳይ ነው።"

"ለተማሪዎች መገልገያዎቹን ስትሰጣቸው ያንን እውቀት በመጠቀም በአካባቢው ላሉ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ ይጀምራሉ።"

የፈጠራ ሰው የፈጣራ ሰዎችን እያፈራ? "ጥሩ ይመስላል" ይላል በፈገግታ። "አባቴ ቢኖር ኖሮ በእርግጠኝነት ይኮራ ነበር።"

ይህ የቢቢሲ ተከታታይ ክፍል የተዘጋጀው ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ታዳጊዎች ፈጠራ ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርገው ቦርሳ

ተያያዥ ርዕሶች