2010 ለታምራት ላይኔ፣ ለእስክንድር ነጋ፣ ለሃጫሉ ሁንዴሳ . . .

ለእኔ 2010 ዓ.ም...

ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ያልተጠበቁ በርካታ ነገሮች ሲከሰቱ በተቃራኒው ይሆናሉ የተባሉ ሳይሆኑ የቀሩ ብዙ ነገሮችም ይኖራሉ። የስልጣን ማማ ላይ የነበሩ ሲወርዱ እስከ ዛሬ የት ነበሩ የተባሉም ስልጣን ተቆናጠዋል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተፎካካሪ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ግለሰቦችና ተቋማት የለውጥ አጋር ናችሁ ወደ አገራችሁ ግቡ ቤት ለእንቦሳ ተብለዋል።

መንግሥትን በመቃወም ቅኝት ውስጥ የነበረው ዲያስፖራ ለመንግሥት አለኝታነቱን ሲያሳይ፤ የረዥም ጊዜ ባላንጣ ኤርትራ የኢትዮጵያ መሪዎች በተደጋጋሚ ጎራ የሚሉባት ሁነኛ ጎረቤት የሆነችበት ዓመት ከመሆኑና ከሌሎችም ነገሮች አንፃር ዓመቱ አገሪቱ በለውጥ ማዕበል ውስጥ የነበረችበት ነው ሊባል ይችላል።

የዓመቱ የቢቢሲ አማርኛ ተነባቢ ዘገባዎች

ብዙ ነገር በሆነበትና ብዙ በተባለበት ባለፈው ዓመት በተለያየ ምክንያት የህዝብ እይታ ውስጥ የገቡ ሰዎች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ የተወሰኑትን ዓመቱ ለእናንተ እንዴት ነበር? ብለናቸዋል።

"የአሮጌው ፖለቲካዊ አመለካከት ሞት የተበሰረበት ነው" የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ ታምራት ላይኔ

ያለፈው 2010 ዓ.ም ብዙ ነገሮች የተከናወኑበት ነው። ያለፈው ሥርዓት ከነችግሮቹ ማለፍ መሞት እንዳለበት ህዝቡ በግልፅ ሃሳቡን ፍላጎቱን የገለፀበት ነበር።

የአሮጌው ፖለቲካ አስተዳደር ዘይቤዎችና የፖለቲካ አመለካከቶች መሞት እንዳለበት የተበሰረበት ዓመት ነበር።

አዲስ ነገር በተስፋ ደረጃ የፈነጠቀበት፤ መልካም ጅማሮ የታየበት ዓመት ነው።

ከሁሉም በላይ አዲሱ ጅማሬ ፈነጠቀ የምለው ህዝብ ያለምንም መደናቀፍና ክልከላ ወጥቶ በነፃነት ሃሳቡን የሚገልፅበት እድል መፈጠሩን ነው። ይህ አዲስ ፋናና ተስፋ ነው። ግን ገና ጅማሮ ነው።

ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ረገድ የተጀመረው ነገር በሌሎች ነገሮችም እየቀጠለ ለውጡ እየጎለበተ የሚሄድበት ተስፋ ነው ብዬ ነው የማምነው።

አዲስ ዓመት ከቤተሰብ ጋር ሆኜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳከብር ከ22 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያዬ ነው። 12 ዓመታትን እስር ቤት ከዚያም አስር ዓመታትን አሜሪካ ነው ያሳለፍኩት።

እስር ቤት እያለሁ ለብቻዬ ሻማ አብርቼ ቀኑን አስብ ነበር። አሁን ግን ከቤተሰቦቼ ፣ እናቴም አለች ከዘመድ ከጓደኞቼ ጋር ነው የማሳልፈው።

በአዲሱን ዓመት ካለፉት ዓመታት ስህተቶቹ ተምሮ፤ ጠንካራ ጎኑም ጠንክሮ ወጥቶ የፊቱን የሚያይ ሰው እሆናለሁ ብዬ ነው የማምነው።

የ2010 የጥበብ ክራሞት

በዚህ የወደፊቱ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ለኢትዮጵያ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የሚጠቅም ነገር መስራት የሚፈልግ ለመስራት የሚተጋ ሰው እሆናለው።

አዲሱን ትውልድ ከስህተቴም ከጥንካሬዬም የማስተምር ሰው እሆናለው ብዬ አምናለው።

አዲሱን ዓመት ሳስብ አሁን የታየው ተስፋ ስር ሰድዶ አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መነቃቃት መንፈስ ሰፍኖ ይቺ ሃገር የመጣችበት የድቀት፣ የመከራና የችግር መንገድ ማክተሚያ የመጀመሪያ እርምጃ ይሆናል ብዬ እገምታለው።

በዚህ ውስጥ በተለይም አዲሱ ትውልድ ከሁለት የብሄርተኝነት ፅንፍ እንዲጠበቅ አፅንኦት መስጠት እፈልጋለው። ሚዛናዊ አስተሳሰብና ሚዛናዊ ግንኙነት እንዲሆር እመኛለሁ።

እቺ አገር እንደ ኢትዮጵያ አንድ ህዝብ አንድ ሃገር ሆና ጠንክራ እንድትወጣ ባለቀለትና በሞተ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ የኢህአዴግ የቀድሞ መሪዎች ልብ እንዲገዙና ሁኔታውን ቆም ብለው እንዲመለከቱ እፈልጋለው።

"እነዚህ ሰዎች የሚያዞሩኝ ከንቲባ ሊያደርጉኝ ነው እንዴ?" የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ

ለአገራችን የተለየ ዓመት ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ፍቅር ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን አጥብቀን የያዝንበት፤ በፍቅር የተያያዝንበት ነው። ነፃነት የተንፀባረቀበትም ነበር።

አዲስ አበባ ማደግ መኖር ደግሞ በራሱ ፍቅር ነው ብዬ አምናለው። ከተማችን አዲስ አበባ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል ያለባት ሁሉም እንደ አቅሙ ወቶ የሚገባባት በመተባበር የሚኖርባት አስተዋይ ሰላም ወዳድ ህዝብ ያለባት ከተማ ናት። እናም አዲስ አበባ መወለድ፣ ማደግና መኖር እነዚህን ስብዕናዎች ተላብሶ ለማደግ እድል እንደሚሰጥ አምናለሁ።

ባለፉት አስር ዓመታት ከክፍለ ከተማ ጀምሮ ከተማውን ሳገለግል ወደ አምስት የሚሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን የመምራት እድል አግኝቼ ነበር። አንዱን ሴክተር አውቄ የተሻለ ውጤት ማምጣት ምችልበት ደረጃ መድረሴን ሳምን ወደ ሌላ ቢሮ መዘዋወር አለብሽ የሚል ጥያቄ ይነሳ ነበር።

ያልተጠበቁ ክስተቶች የታዩበት ዓመት

አንዳንዴ አዝኜም ባለቅ እል ነበር። ወደ ሚቀጥለው ቢሮ ስሄድ ያለ ምንም ችግር ቶሎ ሥራውን እለምድ ነበር። ቶሎ ቶሎ የተለያዩ ቢሮዎችን እንድመራ ሲደረግ እንዴት ነው እነዚህ ሰዎች ከንቲባ ሊያደርጉኝ ነው እንዴ የሚያዞሩኝ ሁሉ እል ነበር። ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ግን በሆነው ነገር ደስተኛ ነኝ።

2011 ዓ.ምን ሳስብ ትልቅ ተስፋ ይታየኛል እንደ አገር። የህዝባችን ልብ ከመሪዎቹ ጋር ስላለ እጅግ ትልቅ ነገር ይታየኛል።

"ህወሃት በ2010 ዓ.ም የበላይነቱን ያጣል ብዬ አልተበቅኩም" ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

ህወሃት በ2010 ይወድቃል ብዬ በፍፁም አላሰብኩም ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች አልጠበቁም ስለዚህም ትልቅ ክስተት ነው። የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጥያቄ ግን በህወሃት መውረድ ብቻ የሚፈታ አይደለም።

ምንም እንኳ ተስፋ የተጣለበት ዓመት ቢሆን በጣም ብዙ ያላለቀ ነገር አለ። ስለዚህ ያለኝ ቁጥብ ተስፋ ነው። ትልቁ የዲሞክራሲ ጥያቄ አልተመለሰም ወደዛ መግባት ካልቻልን ከለውጡ በፊት ወደ ነበርንበት ከዚያም ወደ ከፋ አደገኛ ነገርም ልንገባ እንችላለን።

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አዲሱ ዓመት የሽግግር መንግሥት የሚመሰረትበት እንዲሆን ነው ምኞቴ። ምክንያቱም ሰላማዊ የዲሞክራሲ ሽግግር ማድረግ የምንችለው በሽግግር መንግሥት ብቻ ነው ብዬ ስለማምን ነው።

ለዚህ ዓይነቱ ከአምባገነናዊ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ደቡብ አፍሪካ ጥሩ ምሳሌ ናት ብዬ አምናለው። ይህን ሂደት የማንከተል ከሆነ እናበላሸዋለን ብዬ እሰጋለሁ። በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ህዝብ የሚተማመንበት የምርጫ ሂደት ይኖራል ብዬ አልገምትም።

የሁላችንንም የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚመልሰው የምንተማመንበት ምርጫ ነው።

ስለዚህ ምኞቴ አዲሱ ዓመት የሽግግር መንግሥት መስርተን፣ የምንተማመንበት መንግሥት ለመመስረትና ነፃ ተቋማት ለመገንባት የሚያስችለን ከዚያም ምርጫ የምናደርግበት መንገድ ውስጥ የምንገባበት እንዲሆን ነው።

"የገባው አሜን፤ያልገባውም ለምን ብሏል" አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ

አሁን ያለው ለውጥ እንዲመጣ የአገራችን ህዝቦች መራር ትግል ያደረጉበትና መጨረሻውም ያማረበት ዓመት ነበር። እኔም ከህዝብ ውጭ ስላልሆንኩ እንደ አንድ የኦሮሞ አርቲስት፤ በሚሊኒየም አዳራሽ ከሶመሌ ክልል ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች እርዳታ ማሰባሰቢያ ፤ ከዚያም ደግሞ ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንኳን ደህና መጡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተጋብዤ ነበር።

በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ ከህዝቤ ጎን መቆም የምችለው በሙያዬ ስለሆነ የማምንበትን መልዕክት ለመሪዎች አስተላልፌአለሁ። ያን ደግሞ የኮነኑኝና ሊጎዱኝ የተንቀሳቀሱ ነበሩ። በተቃራኒው ሃላፊነት ተሰምቷቸው የተከላከሉልኝ የመንግሥት ሃላፊዎችም ነበሩ።

ለፕሬዘዳንት ኢሳያስ የተዘጋጀው ፕሮግራምም እንኳን ደህና መጡ ለማለት ቢሆንም ዜጎች በሐረር አካባቢ በግፍ እየተገደሉ ስለነበር እዚያ ቦታ ላይም መልዕክቴን በማስተላለፍ ሙያዊ ግዴታዬን ተወጥቻለው (ያልተጠበቀ ነበር አድርጌያለሁ)።

በሁለት መድረኮች ላይ ያደረግኩትን የገባው እንደገባው አሜን ሲል ያልገባውም ለምን ብሏል። ሁሉም ሃሳቤን ይወደዋል አይወደውምም አልልም።

አዲሱን ዓመት ሳስብ አሪፍ ነገር ነው የሚታየኝ። መንግሥት በዚሁ ከቀጠለ ህዝብም የሚደማመጥና የሚቻቻል ከሆነ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለአገራችን ህዝቦች ተስፋ የሚሰጥ ነው። ከጥቂት ወራት በፊት መንግሥት እንደ መንግጅት ተስፋ የሚጣልበት ሳይሆን የሚፈራ ነበር።

ህዝብ እንደፈለገው ሃሳቡን የሚገልፅበት እምነቱን የሚያንፀባርቅበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ይህ ደግሞ ያስደስተኛል ግን ለዘለቄታው የመንግሥት አምባገነንነትን ስንፈራ ህዝብ አምባገነን እንዳይሆን እሰጋለሁ።

"የእግዚአብሄርን እጅና መልካምነትን ያየሁበት ጊዜ ነው" የቀድሞ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክትር አቶ መላኩ ፈንታ

ዓመቱን ለሁለት ከፍዬ ነው የማየው። ከግንቦት ወር በፊት እስር ቤት የነበርኩበትን እና ከወጣሁ በኋላ ያለውን ማለት ነው። ብዙ ሰዎች እስር ቤት ያለ ሰው ምንም የማያደርግ ቢመስለውም አንድ አይነት ቢሆንም የፀሎት፣ የስፖርት፣ የንባብ እንዲህ እንዲህ እያለ ለሁሉም እቅድ አለው። የእስር ጊዜዬን እንደዚያ ነበር ማሳልፈው።

አልፎ አልፎ ውጭ የሚካሄደውን ነገር መስማት ተስፋ የሚሰጥ ነበር። ከተፈታሁ በኋላ ያለው ለእኔ ባብዛኛው የእግዚአብሄር እጅና መልካምነትን ያየሁበት ጊዜ ነው።

የህዝብን ፍቅር፣ መልካምነትና ፈራጅነትም ያየሁበት ነው። ከሚገባኝ በላይ የህዝብን ፍቅርና ክብርም ያገኘሁበት ነው።

ዓመቱ ከአገር አንፃርም ታሪካዊ ክስተት የታየበት ነው ብዬ ነው የማምነው። ህዝብ በተለይም ወጣቱ ለዲሞክራሲንና ለፍትህ ቆርጦ የተነሳበትም ጊዜ ነበር።

ለውጡ በህዝብ የመጣ ስለሆነ በአዲሱ ዓመት ተስፋ ነው የሚታየኝ። የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገው ጥረት ወደ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲያመራ የሚደረግበትና የሃሳብ የበላይነት የሚነግስበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለው።

በልማትም እኩልነትና ተጠቃሚነት የምናይበት ይሆናል ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው።

ተያያዥ ርዕሶች