በደቡብ አፍሪካ የግድያ ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሚኒስትር በሄኪ ቼሌ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የፖሊስ ሚኒስትሩ በሄኪ ቼሌ

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በየዕለቱ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር 57 መድረሱን የሃገሪቱ ፖሊስ ለፓርላማ ባቀረበው በቁጥር በተደገፈ ማስረጃ ይፋ አደረገ።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሚኒስትር በሄኪ ቼሌ የቁጥሩን ከፍተኛ መሆን በተመለከተ ሲናገሩ የግድያው መጠን በጦርነት ቀጠና ከሚያጋጥመው ጋር የተቀራረበ ነው ብለዋል።

ለግድያ ወንጀሎች መበራከት እንደ ዋነኛ ምክንያት የቀረቡት ከወሮበላ ቡድኖች ጋር የተያያዙ የበቀል ድርጊቶች፣ የቡድንና ፖለቲካዊ ግድያዎች ናቸው።

ማንዴላን ውትድርና ያሰለጠኑት ኢትዮጵያዊ

6 ሚሊዮን ብር፡ በማንዴላ እሥር ቤት ለማደር

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፖሊስ ሚኒስትሩ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለው ወንጀልን የመዋጋት፣ የመከላከልና የደህንነት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም ግድያንና አስገድዶ መድፈርን የመሳሰሉ የወንጀል ድርጊቶች እየጨመሩ መጥተዋል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሴቶች የተገደሉ ሲሆን፤ ገዳዮቻቸውም የሚያውቋቸው ሰዎች ናቸው።

የጦር መሳሪያና ስለት በግድያዎቹ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ግድያዎች የተፈፀሙት በእነዚህ መሳሪያዎች ነው።

በአንድ የበጀት ዓመት ውስጥ ከ20 ሺህ የሚልቁ ሰዎች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተገደሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 62ቱ ብቻ ናቸው በእርሻ ስፍራዎች ላይ የተገደሉት።

የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ምንም እንኳን የግድያ ወንጀሎች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እየጨመሩ ቢሆንም ድብደባ እና ተራ የዝርፊያ ወንጀሎች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ መቀነሳቸው ተገልጿል።

የፖሊስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈፀሙት ወንጀሎች ቁጥር ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት ጨምሯል።

በደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ ፖሊስን የሚቆጣጠረው ኮሚቴ ሰብሳቢ ፍራንሲስ ቡክማን የሁኔታውን አሳሳቢነት ሲገልፁ "ፍፁም ተቀባይነት የሌለውና አሳሳቢ" ብለውታል።

የፖሊስ ሚኒስትሩ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ጠንክረው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች