'ልጅ ብወልድ ብዬ እመኛለሁ' አፈንዲ ሙተቂ

Image copyright አፈንዲ ሙተቂ

በከፍተኛ ቁጥር የተወደደልህ 'ፖስት'

እ... ትንሽ ቆይቷል… 'ኢትኖግራፊ' ስጽፍ በርካታ ተከታዮቼ ይወዷቸዋል፤ በአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዙርያ የጻፍኩት እስከ 8ሺህ የሚሆኑ ውዴታዎችን አግኝቷል።

በዝቅተኛ ደረጃ የተወደደ

ኸረ ብዙ ነው! በተለይ እንደ ጀመርኩ ሰሞን 10 ሰው ብቻ የሚወደው 'ፖስት' ነበር፤ ጽሑፉን በመጥላት ሳይሆን ብዙ ተጠቃሚ ባለመኖሩ።

እጅግ አስቂኙ አስተያየት

ባለፈው 'አዳል' የሚል የታሪክ መጽሐፍ ጽፌ ነበር፤ አንዱ 'ኮሜንት' ላይ እንዲህ አለ፣ "አሕመድ ግራኝ ከትግራይ ወደ ሐረር ተሰደው የመጡ መሆናቸውን ገልጸኻል፤ ስለዚህ የመጽሐፍህን ርዕስ በዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ስታይል 'የትግሬና የአደሬ እውነተኛ የዘር ምንጭ' ማለት ነበረብህ' ያለኝ በጣም አስቆኛል።

የምትወደው 'ፌስቡከር'

ብዙ ናቸው፤ ዶ/ር እንዳላማው አበራን ግን የሚያህልብኝ የለም።

አወዛጋቢ 'ፖስት'

የሚያወዛግቡ ጽሑፎችን አልጽፍም፤የኔ ስታይልም አይደለም፤ የኔ ዓላማ ሰዎች እንዲቀራረቡ ስለሆነ የሚያወዛግብ ጉዳይ ቢኖርም ከመጻፍ ራሴን አቅባለሁ።

Image copyright ቢቢሲ

እጅግ ያልተጠበቀ የውስጥ መስመር መልዕክት

(ሳቅ)... የሚሳደበውን ትተን 'እስኪ ይህችን የሞባይል ካርድ ሙላት ከሚል ጀምሮ 10 ሺህ ብርና ላፕቶፕም የሸለመኝ አለ።

ፌስቡክ ሳታይ የቆየህበት ረጅም ጊዜና ምክንያት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ ሲታወጅ ኢንተርኔት ተቋርጦ ስለነበር ለአንድ ወር ተኩል ያህል ጠፍቼ ነበር። ከመረጃ መራቁ ቢከብድም፤ ወደ ንባቡ በጣም አተኩር ነበር።

ከማኅበራዊ ሚዲያው ምን አተረፍክ?

እንደሚታወቀው ፌስቡክ የሚጠቀሙት አፍላ ወጣቶች ናቸው፤ ስሜታዊነት ይንፀባረቅበታል፤ ብዙም ሐሳብ የሚሰጥ ነገር የለውም፤ ግን ከሰው ጋር አስተዋውቆኛል።

ከፌስቡክ ጡረታ የምትወጣበት ዘመን

እ....ፈጣሪ ነዋ የሚያውቀው! ግን መውጣቴ አይቀርም፤ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አጠቃቀሙን መቀየር አስባለሁ፤ የጊዜ ገደብ ግን አላስቀመጥኩም።

በ70 ዓመትዎ ፖስት ሊያደርጉት የሚችሉት ሐሳብ

ከዛሬ 30 ዓመት በኋላ? አሁን እኮ 40 ዓመቴ ነው! እ... አይ መኖሬንም እንጃ! (ረዘም ያለ ፋታ) ወይ እንደ ዶናልድ ትራምፕ... (ሳቅ) በጣም ከባድ ጥያቄ ነው... እኔንጃ እንግዲህ....

ፌስቡክን የሚመለከቱበት ፍጥነት

በአማካይ በቀን አራት ጊዜ ያህል አያላሁ ፤ፖስትም አደርጋለሁ።

ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ምን አጣህ?

ጊዜ ይገድላል፤ በፊት መጽሐፍ ንባብ ላይ ነበር የማተኩረው፤ አሁን እሱም እየቀረ ነው። ትኩረትን ይሰርቃል፤ የሰውን ሐሳብ ይሰርቃል፤ እንደውም አንዳንዴ ሱስ ይሆናል። አይንም ይጎዳል ፤ አሁን የርቀት ዕይታዬ እየቀነሰ ነው።

2010ን በአንድ መስመር

ቱርክን መጎብኘቴ አስደስቶኛል። የመንግሥት ለውጡም አስደስቶኛል። ለተሻለ ሕይወትና ነጻነት ሲታገሉ ዜጎች መሞታቸው ልቤን ነክቶታል።

የ2011 ምኞት በአንድ መስመር

ልጅ ብወልድ ብዬ እመኛለሁ።