በአርባ ምንጭ የሐገር ሽማግሌዎች ውድመትን ተከላከሉ

የአርባ ምንጭ የሐገር ሽማግሌዎች ርጥብ ሳር ይዘው Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ የአርባ ምንጭ የሐገር ሽማግሌዎች ርጥብ ሳር ይዘው ያደረጉት የመጨረሻ ተማፅኖ

በጋሞ ባህል መሰረት ማንኛውም ሰላምን የሚያደፈርስ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ረብሻ፣ ግጭት በሚኖርበት ጊዜ፤ ሁኔታውን ለማብረድና ለመፍታት የሐገር ሽማግሌዎች ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ነው።

በባህሉ መሰረት በተለይ በርካታ ህዝብ ባለበት ቦታ፤ ህዝብ መደማመጥ፣ መነጋገር፣ መግባባትና 'አንተም ተው፤ አንተም ተው' ማለት በማይቻልበት ቦታ ላይ የትኞቹም የባህል አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች እርጥብ ሳር አሊያም ቅጠል ይዘው ከቆሙ ማንኛውም የሚደረግ እንቅስቃሴ ይቆማል።

መደማመጥ፣ መነጋገር ይጀመራል፤ ይህም ሲወርድ ሲወራረድ የመጣና ማህበረሰቡ ሰላምን የሚያረጋግጥበት እሴት ነው።

ሳር፤ አሊያም እርጥብ ቅጠል የሰላም ምልክት ሲሆን ሰላም ማውረድ፣ ረብሻና ብጥብጡን ማቆም የሚል ትርጓሜ አለው።

በሳምንቱ የመገባደጃ ቀናት በኦሮሚያ ክልል ፊንፈኔ ዙሪያ ልዩ ዞን አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካቶች ለሞት ሲዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩት ቀያቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ናቸው በተባሉትና አሸዋ ሜዳ፣ ከታ፣ ቡራዮ አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች የንብረት መውደምና ዝርፊያ መፈፀሙም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ባጋጠመ ግጭት 5 ሰዎች ተገደሉ

ስለተፈፀመው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው

ድርጊቱ በርካቶችን ያስቆጣ ነበር። በዚህም በአዲስ አበባና በአርባምንጭ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ በነቂስ የወጣው ወጣትም በአካባቢው በወገኖቹ ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያና የደረሰው እንግልትን አውግዟል።

በአካባቢው የሚገኙ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ላይ ድንጋይ በመወርወር ስሜታቸውን የገለፁም ነበሩ።

ሁኔታው ያላማራቸው የአገር ሽማግሌዎች በጋሞ ባህል መሰረት የባሰ ጉዳት ሊደርስባቸው በነበሩት ንብረቶች ፊት ለፊት በመንበርከክና እርጥብ ሳር በመያዝ በቁጣ የገነፈለው ወጣት ከጥቃት ራሱን እንዲያቅብ አረጋግተዋል።

ስለተፈፀመው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው

በአካባቢው የአገር ሽማግሌ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሰዲቃ ስሜ፤ "የሰላማዊ ተቃውሞው ዓላማ ንብረት ማውደምና በሰው ላይ ጥቃት ማድረስ አልነበረም፤ ሙከራው እንዳለ ስናይ የባንኮቹን ጠባቂዎች በማግባባትና ርጥብ ሳር ይዘን በመንበርከክ ወጣቱ ከድርጊቱ እንዲታቀብ አድርገናል" ይላሉ።

እኝህን የአገር ሽማግሌ ባነጋገርናቸው ሰዓት ጥቃት ሊደርስባቸው በነበሩት ባንኮች ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን እያረጋገጡ እንደነበር ነግረውናል።

Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ በአርባ ምንጭ የሐገር ሽማግሌዎች ርጥብ ሳር ይዘው

በተቃውሞው ወቅት ከወጣቶቹ መካከል ነበርኩ ያለን ገነሻ ማዳ "በጋሞ የለቅሶ ባህል በጭፈራ መልክ ለሞቱት የሚያለቅሱ ነበሩ፤ በሌላ በኩል የተፈፀመው ድርጊት አግባብ አይደለም፤ ጋሞ ሰው አይገድልም፤ ቢበደል እንኳን ይቅር ይላል የሚሉ ድምፆችን በጋሞኛ ሲያሰሙ ነበር" ብሎናል ።

በዚህ ሰዓት ድንጋይ በመያዝ ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩት ወጣቶች የሃገር ሽማግሌዎች ተንበርክከው ባደረጉት የመጨረሻ ተማጽኖ በርዷል።

በባህሉ መሰረት ይህንን ልመና የተላለፈ እርግማን ይደርስበታል ተብሎ ስለሚታመን ወጣቱ ይህንን ከመተላለፍ ተቆጥቧል።

በመሆኑም እንደተፈራው በንብረትና በሰው ላይ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ አልፏል፤ አደባባይ የወጣው ህዝብም ተቃውሞውን በሰላም ገልፆ ወደየመጣበት ተመልሷል በማለት ይናገራል።

'በእኔ በኩል ሒሳቤን ዘግቻለሁ ' አቶ ታምራት ላይኔ

ሌላኛው ያነጋገርናቸው የሐገር ሽማግሌ አቶ አንጀሎ አርሾ በጋሞ ተወላጆች ላይና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ጥቃት፣ መደፈር፣ ንብረት ማውደምና ላይ የደረሰው በደል በማውገዝ ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቷል" ይላሉ።

በጋሞ የለቅሶ ባህል መሰረትም በእንብርክክ እየሄዱ በርካቶች ሃዘናቸውን ሲገልፁ ነበር።

ይሁን እንጂ ሁኔታውን ወደ ሌላ ብጥብጥ ለማሸጋገር የሚሞክሩ እንደነበሩ ያልሸሸጉት የአገር ሽማግሌው፤ "በአርባ ምንጭ ከተማ በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ተነሳስተው ፊት ለፊት ያገኟቸውን ባንኮችና የግለሰብ ቤቶች ለመግባት ወጣቱ ገንፍሎ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፤ በጋሞ ባህላዊ ሥርዓት ተማፅኖና ልመና ሁኔታውን በሰላማዊ ሁኔታ ለማለፍ ተችሏል" ብለዋል።

በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይም ጉዳት እንዳይደርስ በጋሞ ሽማግሌዎች የተደረገው የመከላከል ሥርዓት ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

በተፈናቃዮች ብዛት ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚ ሆነች

ቄሮ፣ ሴታዊት፣ ፋኖ…የትውልዱ ድምጾች

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ገበየሁ ጣራ በበኩላቸው ህዝቡ በጋሞ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ህጋዊ ጥያቄ ያቀረበና ፈቃድ እንደተሰጠው ገልፀዋል።

ነገር ግን በመካከላቸው የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ወደ ስታዲየም በመሄድ ፋንታ ንብረት ለማውደም ያመሩት እንደነበሩ ይናገራሉ። የፀጥታ ኃይሎችም ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ወደ ሰማይ ሲተኩሱ እንደነበር ተናግረዋል።

በዚህም ወቅት በባረቀ ጥይት የ2 ሰዎች ሕይወት ሲያፍ፤ 3 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሶዶ ሆስፒታል ተልከው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በንብረት ላይ የደረሰ ውድመት አለመኖሩን ተናገሩት ኃላፊው አጋጣሚውን በመጠቀም ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ ገበየሁ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በከተማዋ ዛሬ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩና በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ