በቡራዩ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የባንክ ሂሳብ ውስጥ 8 ሚሊዮን ብር ተገኘ፡ ዶ/ር ነገሪ

ነገሪ ሌንጮ

በቡሩዩ እና አካባቢዋ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉ ግለሰቦች የባንክ ሂሳብ ውስጥ 8 ሚሊዮን ብር መገኘቱን መንግሥት ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ገንዘብ በመመደብ የሕብረተሰቡን ሰላም ለማወክ ከአዲስ አበባ ጀምሮ የተንቀሳቀሰ ቡድን አለ ብለዋል።

«የቡድኑ አባላት 99 ግለሰቦች ናቸው» ያሉት ደ/ር ነገሪ፤ የቡድኑ አባላት የሆኑ ግለሰቦች የጦር መሳሪያ፣ ተሽከርካሪ፣ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች እና የቡራዩ ከተማ መሬት አስተዳደር ሀሰተኛ ማህተም ይዘው በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።

አባላቱ ሃሰተኛ የብር ኖቶችን ጨምሮ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ጥሬ ገንዘብ መያዙን እና በቁጥጥር ሥር በዋሉ ግለሰቦች የባንክ የሂሳብ ቁጥር ውስጥ 8 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒሸኬሽን ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ጨምረው ተናግረዋል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል ምረመራ የተጠናቀቀባቸው ተጠርጣሪዎች በቅርቡ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ጨምረው ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች