የወጣቶች ጅምላ እሥር በአዲስ አበባ

ጅምላ እሥር በአዲስ አበባ

ዕለተ ረቡዕ መስከረም 8/2011፤ ወ/ሮ መሠለች ተክሌ እና ቤተሰቦቻቸው የ12 ቀን ልጅ ልጃቸውን ትንሽ አመም አርጓት ኖሮ ወደ ሆስታል ያቀናሉ።

ቤተሰቡ ሃገር ሰላም ብሎ፤ ከሆስፒታል ተመልሶ ምሳ ለመብላት ሲሳናዳ ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ።

«የደንብ ልብሳቸውን በወጉ የታጠቁ አራት አምስት የሚሆኑ የፀጥታ ኃይሎች ልጄን አቶ መኮንንን ፍለጋ በክፍት መኪና መጡ» ይላሉ።

«አንድ ጉርሻ እንኳን ይጉረስ ብላቸው እምቢ አሉኝ» ይላሉ ወ/ሮ መሠለች።

የፀጥታ ኃይሎቹና ልጃቸው መኮንን ወደ አሥር ሰዓት ገደማ ወደቤት መጥተው ፖሊሶቹ ፍተሻ እንዳደረጉ ወ/ሮ መሠለች ያስታውሳሉ።

«ለጥያቄ ነው የምንፈልገው ይመለሳል ብለው ነው የወሰዱት» የሚሉት እናት መሠለች ልጃቸው መኮንን ግንቦት 7 ወደ ሃገር ቤት ሲገባ ለማስተባበር የተሰለፈው ኮሚቴ አባል እንደሆነ ያወሳሉ።

ነገር ግን ልጃቸው መኮንን ፍርድ ቤት በቀረበ ወቅት 'ከቡራዩ እና አሸዋ ሜዳ ግርግሮች' ጋር በተያያዘ እንደተያዘ ተነግሮታል ይላሉ።

«እናቴ እና እህት ወንድሞቼ ቡራዩ የተከሰተውን ግድያ በመሸሽ እኔ ጋር ተጠልለው ነው ያሉት፤ እኔ እንዴት እንዲህ ዓይነት ነገር አደርጋለሁ፤ ብሎ ተክራክሯል» በማለት የፍርድ ቤት ውሎውን ያስታውሳሉ ወ/ሮ መሠለች።

3ኛ ፖሊስ ጣብያ መጀመሪያ ላይ ታስረውበት የነበረው ቦታ ለጤና ምቹ ያልሆነ፣ ጨለማ እና የሽንት ሽታ የነበረው እንደሆነ ወ/ሮ መሰለች ነግረውናል።

«አሁን ግን. . .» ይላሉ፤ «አሁን ግን የተሻለ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት» በማለት ያክላሉ። እንደሳቸው ልጅ ላለ የልብ ህመም እና የሳይነስ አለርጂ ላለበት ቀርቶ ለማንም የሚመች እንዳልሆነም ይጨምራሉ።

ከኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ወደ ሃገር ቤት መመለስ ዋዜማ ጀምሮ ሰላም ርቋት የቆየችው አዲስ አበባ ከሰሞኑ ደግሞ በየቦታው በሚስተዋሉ ጅምላ እሥሮች ድንጋጤ ላይ ያለች ትመስላለች።

በፌስቡክ ስሙ Ab Bella የሚታወቅ ሰው ከፈረንሳይ አካባቢ ኳስ በመመልከት ላይ ሳለ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ከሌሎች ሰዎች ጋር በጅምላ እንደታሰረ በገፁ ፅፏል።

ከእሥር በኋላ ነው ሁሉም ከየተያዘበት በቡድን በቡድን ሆኖ እንዲሰለፍ የተደረገው የሚለው አቤል የእሥሩ ዓላማ ሰውን ማስደንበር ሳይሆን አይቀርም ይላል።

ዛሬ ከሰዓት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሠረት ከመስከረም 2 - 7 ባሉት ቀናት 28 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህም መሀከል 7ቱ በፖሊስ የተገደሉ ሲሆኑ አንድ ሰው በስህተት የተገደለ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡

ከዚው ውጭ የሚወጡ መረጃዎች ፖሊስ የሚያውቃቸው አይደለም ሲሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ደግፌ በዲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ፖሊስ ሁከቱን ለማስቆም ባደረገው ሙከራም በህገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው የተገኙ በርከት ያሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሁከቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ 1 ሺህ 204 የሚሆኑ ግለሰቦችን ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰብሰብ በቀጣይ ሌላ ጥፋት ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ሰንዳፋ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ለተሃድሶ ስልጠና ወደ ጦላይ እንዲገቡ መደረጉንም ኮሚሽነሩ አክለዋል።

ኮሚሽነሩ 174 ሰዎች በህግ ይጠየቃሉ፤ ሌሎች ከ1400 በላይ ደግሞ ከሺሻ ቤት እና ቁማር ቤቶች የተያዙና በርካታ ገንዘቦች ያሏቸው ናቸው ብለዋል።

ወ/ሮ መሠለች ልጃቸው በቁጥጥር ሥር ሲውልም ሆነ ፍተሻ ሲደረግበት የፍርድ ቤት ማዘዣ እንዳልነበር ይናገራሉ።

«እግዚአብሔር ካለ መስከረም 24 ገደማ ይፈታል ብለን እንጠብቃለን» ሲሉ ወ/ሮ መሠለች ተሰፋ ያደርጋሉ።