«አዲስ አበባ የሁሉም ናት» አርበኞች ግንቦት 7

የአርበኞች ግንቦት 7 አርማ Image copyright የአርበኞች ግንቦት 7

የአርበኞች ግንቦት 7 የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ድርጅታቸውን የሚመለከቱ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከቢቢሲ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎቸ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን በወንጀል ምክንያት ከሰሞኑ ማሰሩ ይታወቃል።

ከእነዚህ እሥረኞች መካከል የአርበኞች ግንቦት 7 አቀባበል ኮሚቴ አባል የነበረው ብርሃኑ ተክለያሬድ እና ሌሎችም የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች እንደሚገኙበት አቶ ኤፍሬም አረጋግጠዋል (ከቃለመጠይቃችን ጥቂት ሰዓታት በኋላ ብርሃኑ ከእስር ተፈትቷል)።

«ኦሮሞ እና አማራን የሚነጣጥሉ አይሳካላቸውም»

የአርበኞች ግንቦት 7 አቀባበል ኮሚቴ አባል ፍርድ ቤት ቀረበ

«የእኛ ፓርቲ አባላት ብቻ አይደሉም የሌሎች ፓርቲ አባላትም ለእሥር ተዳርገዋል» የሚሉት አቶ ኤፍሬም በጉዳዩ ዙርያ ከመንግሥት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ነግረውናል።

«አባሎቻችን እየተደረገባቸው ያለው ምርመራ እየተጠናቀቀ ነው፤ አሁን ጥሩ መንፈስ ላይ ነው ያሉት» ሲሉ አቶ ኤፍሬም ታሣሪ አባሎቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

«ሂደቱ በአጭር ጊዜ አልቆ አባሎቻችን ቶሎ ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ» ይላሉ አቶ ኤፍሬም።

«በመንግሥት ደረጃ የምንታገለው መንግሥት የለም»

ምነው ግንቦት ሰባት በታሰሩ አባላቱ ዙርያ ዝምታን መረጠ? ብለን ለጠይቅናቸው ጥያቄ አቶ ኤፍሬም ሲመልሱ «ከዚህ በፊት አንድ ክስተት ሲከስተ መግለጫ እንሰጥ ነበር፤ የዚያ ምክንያት ደግሞ ከሃገር ቤት ውጭ ሆነን መንቀሳቀሳችን ነው፤ ትግላችን ከአገዛዙ ጋር ነበር። አሁን ግን ሃገር ቤት ነን፤ በመንግሥት ደረጃ የምንታገለው መንግሥት የለም አብረን የምንሠራው እንጂ» ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም ነግረውናል።

«የምናስቀድመው የተፈጠረው ነገር ምንድነው ብለን ከመንግሥት ጋር መወያየት እንጂ አስቀድመን መግለጫ የምንሰጥበት ሁኔታ ላይ አይደለንም።»

አቶ ኤፍሬም አክለውም «መግለጫ ሳናወጣ ከመንግሥት ጋር የሰራናቸውን ሥራዎች ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ያየዋል» ብለውናል።

ግንቦት 7 ከመንግሥት ጋር ያደረገውን ውይይት እና የውይይቱን ውጤት አሁን ባለበት ሁኔታ ለሚድያ ሊያሳውቁ እንደማይችሉ ነው አቶ ኤፍሬም ያስረዱት።

«አዲስ አበባ የሁሉም ናት»

አምስት የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ማክሰኞ ዕለት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባለ አምስት ነጥብ አቋም መግለጫ አውጥተዋል።

መግለጫው በተለይ በማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

ድርጅቶቹ ካወጧቸው አቋሞች መካከል «አዲስ አበባ የኦሮሞ ሕዝብ ናት፤ ነግር ሁሉም ሊኖርባት ይችላል» የሚለው ብዙዎች ጎራ ከፍለው እንዲነጋገሩ ያደረገ ሆኗል።

"ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ተገንጥሎ የሚወጣ አካል የለም"-ኤፍሬም ማዴቦ

«የሠራዊታችን አባላት በክብር ይሸኛሉ» ግንቦት 7

ሌሎች ደግሞ መግለጫው ግንቦት 7 ላይ የተሰነዘረ ዱላ ይመስላል ይላሉ።

አቶ ኤፍሬም ግን «መግለጫው እኛ ላይ የተሰነዘረ ነው ብዬ አላምንም» ባይ ናቸው። አክለውም «ድርጅቶቹ አዲስ አበባ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ አለኝ የሚለውን ጥያቄ አንስተዋል፤ እርግጠኛ ነኝ ወደፊት ይህንን ጥያቄ ኢትዮጵያዊያን ተመካክረው የሚፈቱት ይሆናል» ሲሉ ያስረዳሉ።

«እስከዛሬ ድረስ ያለውን ብናወራ ግን አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝብ ከየአቅጣጫው መጥቶ ላለፉት 120 ዓመታት የገነባት ከተማ ናት። የአንድ አካባቢ ሕዝብ የገነባው ቦታ አይደለችም፤ የሁሉም እንጂ።»

አቶ ኤፍሬም ከመግለጫው መካከል ሚድያ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እንዳላስደሰታቸው አልሸሸጉም።

«የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሆነ ግለሰብ ሚድያ ጠላቴ ነው የሚል ከሆነ እርሱ ነው የሚድያ ጠላት። ኢሳት የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ነው ተብሎ የተሰጠውን መግለጫ በግሌ አወግዛለሁ።»

አቶ ኤፍሬም አርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵያ ውስጥ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ከሚያራምዱ ኃይሎች መካከል አንዱ ነው ይላሉ።

«ኢትዮጵያ ውስጥ ለላፉት 27 ዓመታት የነገሰውን የጎሳ ፖለቲካ ወይም የማንነት ፖለቲካ የምንለውን ማራማድ የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ የእኛ እዚህ መምጣትና የጠፋ የመሰላቸውን ኢትዮጰያዊነት እንደ አዲስ ማቆጥቆጥ ያስፈራቸው ኃይሎች ናቸው» ሲሉ ይገልፃሉ።

አቶ ኤፍሬም «ግንቦት 7 ለሁት ተከፍሏል ተብሎ በተደጋጋሚ የሚነገረው ጉዳይ ርካሽ ፖለቲካ ነው፤ ግንቦት 7 አሁንም አልተከፈለም» ሲሉ አስረግጠዋል።

ተያያዥ ርዕሶች