በካማሼ ዞን ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ የፓሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ነቀምቴ የሚገኙ ተፈናቃዮች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈፀመው ጥቃት እጃቸው አለበት የተባሉ የክልሉ 10 የልዩ ፖሊሰ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ሃላፊ አቶ ታከለ ቶሎሳ ለቢቢሲ ቢናገሩም የቤኒሻንጉል ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ባየታ ግን የክልሉ ፖሊስ በድርጊቱ ውስጥ እንደሌለበት ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስና መከላከያ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሲሞክሩ የታጠቁ ኃይሎች ተኩስ በመክፈት ጉዳት አድርሰውባቸዋል ሲሉ የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ሃላፊ አቶ ታከለ ነግረውናል።

ከጥቃቱ ጀርባ የታጠቁ ኃይሎች እንዳሉ ከቀያቸው የተፈናቀሉና በተለያየ ቦታ ተጠልለው የሚገኙ ግለሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጤና ባለሙያዎች ጥቃት ደረሰባቸው

"ማንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለብቻዬ ሰራኋት ሊል አይቻለውም" ጠ/ሚ ዐብይ

ሮናልዶ "ደፍሮኛል" ያለችው ሴት ከመብት ተሟጋቾች ድጋፍ አገኘች

ዘይነባ የተባሉት ከሳሲጋ የተፈናቀሉ ግለሰብ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን የታጠቁ ኃይሎች ተኩስ እንደከፈቱባቸውና ንብረታቸውን ጥለው እንደሸሹ ገልፀውልናል። "አብራኝ ስትሸሽ የነበረችውን ጓደኛዬን በሚዘገንንና በሚያሰቅቅ ሁኔታ በስለት ተገድላለች " ብለዋል።

መከላከያ ኃይል አስር ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለፁት ኃላፊው እነዚህ በቁጥጥር ስር የዋሉ ኃይሎች የመኖሪያ ቤቶችን ሲያቃጥሉና ንብረት ሲያወድሙ በመታየታቸው እንደተያዙ አስረድተዋል።

ታጥቀው ተኩስ የከፈቱት ሃይሎች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት መሆናቸውንም አክለው ተናግረዋል። ግለሰቦቹ በቤኒሻንጉል ክልል በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ 8 በሚባለው ስፍራ እንደሚገኙም ጨምረው አስረድተዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል አስተዳደሪ አቶ አበራ ባየታ በዚህ ግጭት ፍፁም የክልሉ ኃይል አልተሳተፈም ሲሉ አስተባብለዋል።

አክለውም የክልሉ ልዩ ኃይል በሎጅጋንፎይ ጮጌ ከተማ ላይ ነው ያለው ካሉ በኋላ በቁጥርም ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል ብለዋል። በተጨማሪም "በፍፁም በጥቃት ላይ የተሰማራ የክልሉ ልዩ ኃይል የለንም" በማለት ለምላሻቸው አፅንኦት ሰጥተውታል።

እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች እንዲፈፀም የሚያቀነነባብሩ አካላቶችን በማጣራት መንግሥት አስፈላጊውን ምርመራ በማካሄድ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ ነው ሲሉ የተናገሩት የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ሃላፊ ሁኔታው አሁንም ሙሉ በሙሉ እንዳልቆመና የተፈናቃዮችም ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ አስረድተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ