“ትጥቅ መፍታት ለድርድር አይቀርብም”፡ መንግሥት

አቶ ካሣሁን ጎፌ Image copyright FDRE Government Communication Affairs Office

ትጥቅ መፍታት ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሣሁን ጎፌ ገልጹ።

መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሃገር ቤት የገባው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመንግሥት ጋር ትጥቅ ለመፍታት አልተደራደርንም፤ ትጥቅ የሚፈታም፣ የሚያስፈታም የለም ማለታቸው ይታወሳል።

''ኦነግ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ አገር ቤት ይገባል''

ኦነግ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ማወጁን ገለፀ

መንግሥት ከኦነግ ጋር ካገር ውጭ ሊወያይ ነው

በጉዳዩ ላይ ላይ መግለጫ የሰጡት አቶ ካሣሁን ''ኦነግ ወደ ሀገር የገባው ትጥቅ ፈትቶ ነው። አሁንም ቢሆን የቀረውንም ትጥቅ መፍታት አለበት፤ ካልሆነ ግን መንግሥት የዜጎችን ደህንነትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ ሲል ትጥቅ የማስፈታቱን ሥራ ይሰራል'' ብለዋል።

በመንግሥት የቀረበውን የሠላም ጥሪ ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሃይሎች ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውን ገልጸው፤ ኦነግም ወደ ሀገር ሲገባ 1300 ያህል ጦሩን ትጥቅ እንዳስፈታና ጦሩም ስልጠና እየተከታተለ መሆኑን አክለዋል፡፡

ከኦነግ ጋር በተደረጉ ድርድሮች በሠላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ገብቶ ለመፎካከር መስማማቱ የሚታወቅ ነው ያሉት አቶ ካሣሁን፤ በድርድሩ ወቅት ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ያልተነሳው የመደራደሪያ ጉዳይ ስላልሆነ ነው ብለዋል፡፡

"ሠላማዊ ትግል የሚደረገው በሃሳብ እንጂ በአፈሙዝ ስላልሆነ ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበውና ቀይ መስመር ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስለዚህም ኦነግ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤን መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል ያሉት አቶ ካሣሁን፤ ይህ ካልሆነ መንግሥት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

"በኦነግ በኩል የተገለጸው የቃላት ወለምታ ከሆነ እንዲታረም አቋማቸው ከሆነም እንደገና እንዲያጤኑት" ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ጦር የማስፈታት ሂደቱን የሚከታተል ኮሚሽን እንደሚቋቋም ገልጸው ነበር።