ዋሺንግተን ስቴት የሞት ቅጣትን አገደች

የሞት ቅጣት መቅረቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጮቤ አስረግጧል Image copyright Getty Images

ዋሺንግተን ስቴት የሞት ቅጣትን በማገድ የአሜሪካ 20ኛዋ ግዛት ሆናለች።

የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሊሆንባቸው ሲጠባበቁ የነበሩ ስምንት ሰዎችም ይህን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ ተቀይሮላቸዋል።

ይህ ዜና የሞት ቅጣት ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ሲሟገቱ የነበሩ የሰብአዊ መብት ተሟቻቾችን አስፈንጥዟል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 23 ሰዎች በአሜሪካ ምድር በሞት ተቀጥተዋል። ነገር ግን ዋሺንግተን ስቴት እንደ ጎርጎሮሲያዊየኑ ከ2010 ጀምሮ አንድም የሞት ቅጣት ተፈጻሚ አላደረገችም።

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ

"ለወታደራዊ ደኅንነቱ የማንቂያ ደወል ነው" የቀድሞ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን

ረጅሙ የአውሮፕላን በረራ ስንት ሰዓት ይፈጅ ይሆን?

የዋሺንግተን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞች በ1996 አንዲትን ሴት ደፍሮ የገደለ የሞት ፍርደኛን ይግባኝ ባዩበት የፍርድ ሸንጎ ነው ሞት ቅጣት ተፈጻሚ መሆን እንደሌለበትና እስከናካቴው እንዲቀር የወሰኑት።

በሞት ፍርደኛው የቀረበው ይግባኝ የሞት ፍርደኞች በዘር መድሎ የተነሳ የሚፈጸምባቸው የግፍ ቅጣት ስለመሆኑ ጥናት አካቷል። አባሪ የተደረገው ጥናቱ እንደሚያሳየው ከነጭ ፍርደኞች ይልቅ ጥቁሮች ላይ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ ይደረጋል።

ይህን ተከትሎ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞቹ በአንድ ድምጽ እንደወሰኑት የሞት ፍርድ በኅብረተሰቡም ኾነ በፍርደኛው ላይ የሚያሳድረው ምንም ትርጉም ካለመኖሩም በላይ በዘር መድሎ የሚፈጸምበት አግባብ በርካታ ነው።

የሞት ፍርድ መቅረት የለበትም የሚሉ ወገኖች ቢያንስ እጅግ የከፋ ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ሞት ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ይሞግታሉ።