ሙሽሪት እጮኛዋ መቃብር ላይ ድል ባለ ሠርግ ተሞሸረች

ጄሲካ ሐዘን ቢሰብራትም እጅግ ለምታፈቅረው እጮኛዋ ክብር ስትል ሰርጓን በመቃብሩ ላይ ደግሳለታለች Image copyright MANDI KNEEP/LOVING LIFE PHOTOGRAPHY
አጭር የምስል መግለጫ ጄሲካ ሐዘን ቢሰብራትም እጅግ ለምታፈቅረው እጮኛዋ ፍቅር ስትል ሠርጓን በመቃብሩ ላይ ደግሳለች

ነገሩ ፊልም እንጂ በእውን የኾነ አይመስልም።

ኬንዳል መርፊ ይባላል። በበጎ ፈቃድ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኛ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ለሥራ ሲሰማራ አንድ ጠጥቶ የሚያሽከረክር ሰው ገጭቶት ገደለው።

ይህ ምን አዲስ ነገር አለው ታዲያ? ሰው እንደሁ በተለያየ መንገድ ይሞታል።

የመርፊን ታሪክ ልዩ የሚያደርገው ጄሲካን ጥሎ መሞቱ ነው።

የሞተው እጅግ ለሚወዳት እጮኛው ጄሲካ ቀለበት አድርጎላት፤ ቬሎ ተከራይተው፤ የሠርጉ ቀን ተቆርጦ፣ ለፎቶ አንሺ ተከፍሎ፣ ሊሙዚን ተከራይተው መሆኑ ነው ልዩ የሚያደርገው።

Image copyright LOVING LIFE PHOTOGRAPHY

የ25 ዓመቷ ጄሲካ በሐዘን ተኮራምታ ቀረች። ደግሞ እንደሚባለው ፍቅራቸው ለጉድ ነበር። ከዐይን ያውጣችሁ የሚባሉ በአንድ ላባ የሚበሩ ወፎች።

አንድ ሰፈር ቢያድጉም የተገናኙት የኮሌጅ ተማሪ ሳሉ ነበር።

ሁለቱም የለየላቸው የአሜሪካን እግር ኳስ ቲፎዞዎች ነበሩ። አንድ ቀን ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ኬንዴል ኖተርዳም ስቴዲየም ውስጥ መሐል ሜዳ ላይ ተንበረከከ። የ"ታገቢኛለሽ" ጥያቄን ለጄሲካ አቀረበላት። አለቀሰች። በደስታ አለቀሰች ጄሲካ።

Image copyright JESSICA PADGETT
አጭር የምስል መግለጫ ጄሲካ ከእጮኛዋ የ 'ታገቢኛለሽ' ጥያቄ ሲቀርብላት

ከዚያ በኋላ ለሠርጋቸው ቀን ተፍ ተፍ ማለት ጀመሩ። በዚህ መሐል ነበር ሙሽራው ኬንዳል ድንገተኛው የመኪና አደጋ ደርሶበት እስከወዲያኛው ያሸለበው።

ጄሲካ የርሱን ደግነት ተናግራ አትጠግብም። "እጅግ አፍቃሪ፣ እጅግ አዛኝ፣ ድንቅ ሰው...ነበር" ትላለች በእንባ።

ሐዘን ከልቧ ሳይወጣ የሠርጉ ቀን ደረሰ። ለካንስ ሊጋቡ ነበር።

ጄሲካ ይህን ልዩ ቀን እንዲሁ በእንባ እየተንፋረቀች ማሳለፍ አልፈለገችም። የሠርጉ ዝግጅት እንዲቀጥል ወሰነች። ሚዜዎቿ "አብደሻል?' አሏት። አልሰማቻቸውም። አንዲትም ነገር ሳትጓደል የሠርጉ ዝግጅት ቀጠለ።

ሴፕቴምበር 29 ቬሎዋን ለብሳ፣ አምራና ተውባ ብቅ አለች።

ፎቶ አንሺው ሙሽሪትን ከተለያየ ማዕዘን ፎቶ ማንሳቱን ቀጠለ።

ሠርገኛው ጉድ ለማየት ብሎ ይሆን እርሷን ላለማስቀየም ብቻ ብዙዎቹ ተገኝተው ነበር።

በቬሎ እንደደመቀች ወደታዳሚው ዞረች፣ ወደ መድረኩ ወጣች። ለሟች እጮኛዋ ያላትን ፍቅር ተናገረች። ሰዎችም እየተነሱ ስለርሱ ደስ ደስ የሚሉ ወሬዎችን እያወሩ ሳቁ፣ አለቀሱ፣ ተጫወቱ። መደነስ ያለበትም ደነሰ፣ በላ፣ ጠጣ።

ጄሲካም ከአባቷ ጋር ዋልዝ ደነሰች።

Image copyright MANDI KNEPP/LOVING LIFE PHOTOGRAPHY

ለምን ይህን እንዳደረገች ስትጠየቅ "መቼም ባሌ ከሞት ይነሳል ብዬ አይደለም። ጥንካሬዬን ለኔም ለሌሎችም ለማሳየት፣ ፍቅሩም ህያው መሆኑንም ለመመስከር" ብላለች።

ሠርግ ማድረጓ ሕመሟን እንዳቀለለላትም ትናገራለች።

ከሠርገኞቹ መሀል የሙሽራውን/ የባሏን/የእጮኛዋን ባልደረቦች፣ በእሳት አደጋ ብርጌድ ውስጥ አብረውት ይሠሩ የነበሩትን ጓደኞቹን ጠርታቸው ነበር። "ግዴለም ተጣድፋቹ አትምጡ፤ ወንዶች ስትባሉ ሠርግ ላይ ማርፈድ ባሕላችሁ ነው መቼም። " ስትል ቀልዳባቸዋለች።

ታዲያ አንዳቸውም ሠርጉ ላይ አልቀሩም። ግልብጥ ብለው መጡ።

ፎቶ አንሺው ከርሷ ጋር የሚያነሳውን ሰው ፍለጋ ባተተ። የሟች ሙሽራውን ጫማ አጠገቧ አድርጎ ፎቶ አነሳ። ጄሲካ የሙሽራው መቃብር ጋር ፎቶ አንሺ ይዛ በመሄድ ሌላ ፎቶ ተነሳች። ፎቶው የግሏ ሆኖ እንዲቀር ፈልጋ ነበር። ኢንተርኔት ላይ ያዩት ሰዎች ሲቀባበሉት ግን ዓለምን አዳረሰ።

ብዙ ሰዎች ስልክ ደወሉላት። በታሪኩ የተነኩ ሰዎች እያለቀሱ አበረታቷት። ከነዚህ መሀል ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ይገኙበታል።

Image copyright MANDI KNEPP/LOVING LIFE PHOTOGRAPHY

"ፎቶዎቹን ስመለከት እጮኛዬ አጠገቤ ቆሞ ፈገግ ብሎ በፍቅር ሲመለከተኝ ይታየኝ ነበር።" ብላለች፤ ጄሲካ።