ከሃያዎቹ ሚኒስትሮች አስሩ ሴቶች ናቸው

ኢንጅነር አይሻ መሃመድ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር Image copyright Ethiopian Broadcasting Corporation

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛና ሶስተኛ መደበኛ ጉባዔ 410 አባላት በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአዲሱ የካቢኔ ሹመታቸው ከሃያዎቹ ሚኒስትሮች አስሩን ሴቶች አድርገው ሾመዋል።

በዚህም መሰረት ኢንጅነር አይሻ መሃመድ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን በኢትዮጵያም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል።

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የሰላም ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የገቢዎች ሚኒስትር፣ ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር፣ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ ወይዘሪት የዓለም ፀጋዬ አስፋው የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር እንዲሁም ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሆነው ተሹመዋል።

''ታሪክ ተሰራ! አባታችን በጣም ኮርተንብሃል''

"ለወታደራዊ ደኅንነቱ የማንቂያ ደወል ነው"

"ማንም መብታችንን ሊሰጠን ስለማይችል፤ ሴቶች ማንንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መታገል አለባቸው"

የምክር ቤቱን ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ፣ የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ላይ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለማፅደቅና የአፈ ጉባዔዋን መልቀቂያን መቀበልን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል።

በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንን ተግባር የተመለከተውን ረቂቅ አዋጅ አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም የማሻሻያው ሥራ አስተማማኝ ሰላም የማረጋጥ ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ጠንከር ያለ ጥያቄ በመሆኑ፣ ፍትሃዊና ፈጣን ልማት እንዲሁም የእኩል ተጠቃሚነት ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አሟልቶ ለማክበር፣ ከሌብነት የፀዳ ቅን አገልግሎት የመስጠትና የአገልጋይነት ስሜት የተላባሱ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የመንግሥት መዋቅር ሃብት ፈጣሪ የሆነውን የሰው ሃብት ትኩረት ሰጥቶ ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የተሰጠውን ተልዕኮ ማሳካት በሚያስችል አግባብ እንዲደራጅ ሃሳብ ቀርቧል።

"ተቋም ከሁኔታዎች ጋር የሚለዋወጥ ኃላፊነት ያለው፣ የሚወለድ፣ የሚያድግ፣ የሚታመም፣ የሚታከም ደግሞም የሚሞት በመሆኑ ሰዋዊ ባህሪውን ተላብሶ እንዲቀጥል ያለመ ነው" ብለዋል።

ተቋም ማለት ቋሚ ማለት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የተዋቀረው የካቢኔ አደረጃጀት የታሰበውን የእድገት ጉዞ የሚያሳካ እንደሚሆን እምንት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ምክርቤ ቱም የተሻለ አደረጃጀት ውስጣቸውን ፈትሸው አመራራቸውን እንዲያጠናክሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚሰራው ሪፎርም በተሰናሰለና ፈጣን ጉዞ የአስፈፃሚ አካላት የአደረጃጀት ጥናት ለምክር ቤት ቀርቦ በጠቅላይ ሚንስትሩ የቀረበው ስለተደገፈ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ዕድል ተሰጥቷል።

Image copyright Ethiopian Broadcasting Corporation

የተለያዩ ጥያቄዎች ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ስልጣን እና ተግባር ማሻሻያ ረቂቅ ላይ እየቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የደን እና አካባቢ ሚኒስትር ወደ ኮሚሽንነት ዝቅ መደረጉ ኢትዮጵያ እከተለዋለሁ ከምትለው አረንጓዴ ምጣኔ ኃብት ጋር አይጋጭም ወይ? ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መስሪያ ቤቶችን በደንብ የማቋቋም እና የማጠፍ የበዛ ስልጣን አልተሰጠውም ወይ? የሚሉ ይገኙባቸዋል።

የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ቁጥር ከሃያ ስምንት ወደ ሃያ እንዲያንስ የተደረገ ሲሆን ይህም ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናግረዋል።

የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ስልጣን እና ተግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ 1097/211 በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በአዋጁ መሰረት የተቋቋሙት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች 19 ሲሆኑ የፕላን ኮሚሽን ደግሞ 20ኛው የካቢኔ አባል መስሪያ ቤት ሆኖ ፀድቋል፡፡

1. ሰላም ሚኒስትር- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

2. የአገር መከላከያ ሚኒስትር -ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

3. የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር - አቶ አህመድ ሺዴ

4. የግብርና ሚኒስትር -አቶ ኡመር ሁሴን

5. የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር -ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ብረእግዚያብሔር

6. የገቢዎች ሚኒስትር - ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

7. የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር - ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ

8. የትራንስፖርት ሚኒስትር - ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ

9. የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር -አቶ ዣንጥራር አባይ

10. የትምህርት ሚኒስትር -ዶ/ር ጥላዬ ጌቱ

11. የማዕድና ነዳጅ ሚኒስትር- ዶ/ር ሳሙኤል ሁርቆ

12. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር - ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም

13. የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር- ወ/ሪት የአለም ፀጋዬ

14. የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር- ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

15. የባህልናቱሪዝም ሚኒስትር - ዶ/ር ሒሩት ካሳው

16. ጠቅላይ አቃቤ ህግ - አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ

17. የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር - ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

18. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር- ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ

19. የጤና ጥበቃ ሚኒስትር -ዶ/ር አሚር አማን

20. የፕላን ኮሚሽን- ዶ/ር ፍፁም አሰፋ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተሿሚ ሚኒስትሮች ሌብነትን የሚፀየፍ፣ ቅንነት የተሞላበት ስርዓትን የሚዘረጉ እንዲሆኑ ለሰራተኞች ቅርብ እንዲሆኑ የለውጥ ሂደትን (ሪፎርምን) በራሳቸው የሚያመጡ፥ የስራ ሰዓትን የሚያከብሩ ትጉሃን እንዲሆኑ ስቆ ማስተናገድን፣ አገልጋይ መሆንን፣ የሰራተኞችን ሸክም የሚረዱ እንዲሆኑ ፕሮቶኮል የሚያስጠብቁ፣ ስነ ምግባርን የሚያሰርፁ እንዲሆኑስብሰባ በመቀነስና ብዙውን ጊዜ በስራ የሚያሳልፉ እንዲሆኑ መመሪያ ሰጥተዋል።

ከዕለቱ አጀንዳዎች አንዱ የነበረውን የክብርት አፈ ጉባዔዋን የስራ መልቀቂያን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎታል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር የታጠፈ ሲሆን፤ በስሩ ይከወኑ የነበሩ ሥራዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር የሚቋቋም የፕሬስ ቢሮ የሚፈፀሙ ይሆናል።በኮሚሽን ደረጃ የተቋቋሙ ተቋማት ደግሞ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የአካባቢ ደህንነትና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ኮሚሽን፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ናቸው።

ተያያዥ ርዕሶች