ጃፓን ከቀበሌ መታወቂያ ያነሰች ሞባይል ሠራች

በጣም ትንሽዬዋ ሞባይል Image copyright NTT DOCOMO

ጃፓኖች መዳፍ የማትሞላ ስልክ ፈብርከዋል። ከቀበሌ መታወቂያ ይልቅ ለመንጃ ፈቃድ ትቀርባለች። ትክክለኛ መጠኗ ከ "ኤቲኤም" ካርድ አይበልጥም ተብሏል።

ፈብራኪዋ ኤንቲቲ ዶኮሞ የሚባል የጃፓን ቴሌኮም ኩባንያ ሲሆን ይቺን ስልክ በሚቀጥለው ሳምንት ገበያ ላይ አውላታለሁ ብሏል።

በስክሪን ስፋቷ ትንሽ መሆኗ ብቻም ሳይሆን ቅጥነቷም እያነጋገረ ነው። ከ5.3 ሚሊ ሜትር አትወፍርም።

ሞባይል ስልክዎ ላይ መከራን አይጫኑ

የስልክዎን ባትሪን ለረዥም ጊዜ ለመጠቀም

በሌላ አነጋገር በየጎዳናው የምትሸጠዋን የቢዝነስ ካርድ መያዣ ገዝቶ ይቺኑ ስልክ አብሮ ከካርዶቹ መሀል መሰንቀር ይቻላል።

መደወል ሲያስፈልግ ከቢዝነስ ካርዶች መሀል እንደ ቀበሌ መታወቂያ መዘዝ ማድረግ ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ይህቺ ስልክ በክብደትም ቢሆን አትታማም። ከ47 ግራም በላይ አትመዝንም።

ሚጢጢዋ ስልክ ለመጠኗ የማይመጥን ስም የተሰጣት ይመስላል፤ ኬዋይ-01ኤል ትባላለች።

በሞባይልዎ የኢንተርኔት ወጪ ተማረዋል?

ሞባይል ለእናቶችና ለህፃናት ጤና

ትልልቅ ስልክ መያዝ ምርጫቸው ላልሆኑ ደንበኞች ብቻ ሳይሆን ትልቅ ስልክ ኖሯቸው ነገር ግን አንድ ተጨማሪ ስልክ መያዝ ለሚፈልጉ ሁነኛ ምርጫቸው ትሆናለች ተብሏል።

አምራቿ ኤንቲቲ ዶኮሞ ቴሌኮም ይቺን ስልክ "የዓለማችን ጢኒጥዬዋ ስልክ" ሲል አቆላምጧታል።

በ2016 ዓ.ም ሞቶሮላ ባለ 5 ሚ.ሚ ውፍረት ያላትና ጥብቅ ባለ ጂንስ ሱሪ ኪስ ሹልክ ብላ የምትገባ ስልክ ማምረቱ ይታወሳል።

በቀጣይ ሳምንት ለገበያ የምትቀርበው ጢኒጧ ስልክ 32ሺህ የጃፓን የን ታስከፍላለች፤ ወደ ኪስ ስትገባ የምትቀለዋ ስልክ ስትገዛ ግን ኪስ ትጎዳለች። 32 ሺህ የን ወደ ብር ሲመነዘር ከ8ሺህ አያንስም።