ከኤልን ጆንሰን ሰርሊፍ እስከ ሣህለወርቅ ዘውዴ - የዓለማችን ሴት መሪዎች

ሳህለወርቅ ዘውዴ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝደንት አግኝታለች፤ በፕሬዝደንትነት ማዕረግ ሲሆን በሃገሪቱ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥት ከ20 የካቢኔ አባላት አስሩን ሴቶች አድርጎ በመሾም መነጋገሪያ የሆነው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ነበር።

በያዝነው ሳምንት ደግሞ አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር አድርጎ በመሾም አፍሪካና የተቀረውን ዓለም ማነጋገር ችለዋል።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝደንቷ የላቀ ሥልጣን ቢኖውም አሁን ላይ አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ቦታ በመያዝ ሣህለወርቅን የሚስተካከላቸው የለም።

የላይቤሪያ ፕሬዝደንት የነበሩት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ አህጉረ አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን በመጨበጥ ሃገራቸውን ለበርካታ ዓመታት መርተዋል።

ነገር ግን በቅርቡ ለታዋቂው እግር ኳሰኛ ጆርጅ ዊሀ ቦታውን በሰላማዊ መንገድ በመልቀቅ ተሰናብተዋል።

የብራዚሏ ዲልማ ሩሴፍም ስማቸው የሚነሳ ነው፤ ምንም እንኳ ሙስና ስማቸው ተብጥልጥሎ ሥልጣን ቢለቁም።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተሰኘው የዜና ወኪል ከሆነ አሁን ላይ 17 ሴቶች በርዕሰ-ብሔርነት አሊያም በርዕሰ መንግሥትነት ያገለግላሉ።

አዲሷ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ይህን መዝገብ የተቀላቀሉ ግለሰብ ሲሆኑ ቁጥሩን ወደ 18 ከፍ አድርገውታል።

በምጣኔ ሃብት ከፈረጠሙቱ መካከል የጀርመኗ መራሄ መንግሥት ኤንግላ ሜርክል እና የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ይጠቀሳሉ።

ዓለማችን ካሏት ሴት መሪዎች መካከል 10 ያህሉ የመወሰን መብት ያለውን ሥልጣን የጨበጡ ሲሆን ይህም ከጠቅላላው 5.6 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል።

የፎቶው ባለመብት, Paul Morigi

• እነሆ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ ሴት የሃገራት መሪዎች፤ (የዘመናቱ አቆጣጠር በአውሮፓውያን መሆኑ ልብ ይባል)

• ሸይክ ሃሲና - የባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ

• ከርስቲ ካሊጁሌድ - የኢስቶኒያ ፕሬዝደንት፤ ከፈረንጆቹ ጥቅምት 2016 ጀምሮ

• ካትሪን ጃኮብስዶቲር - የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከፈረንጆቹ ህዳር 2017 ጀምሮ

• ዳሊያ ግሪባውስካይት - የሉቴኒያ ፕሬዝደንት፤ ከግንቦት 2009 ጀምሮ

• ማሪ-ሉዊ ኮሌይሮ ፕሬካ - የማልታ ፕሬዝደንት፤ ከነሃሴ 2014

• ሂልዳ ሄይን - የማርሻል ደሴቶች ፕሬዝደንት፤ ከጥር 2016 ጀምሮ

• ሳራ ኩጎንጌልዋ - የናሚቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከመጋቢት 2015 ጀምሮ

• ቢዲያ ባንዳሪ - የኔፓል ፕሬዝደንት፤ ከጥቅምት 2015 ጀምሮ

• ጃሲንዳ አርደርን - የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከጥቅምት 2017 ጀምሮ

• ኤርና ሶልበርግ - የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከመስከረም 2013 ጀምሮ

• መርሰዲስ አራዎዝ - የፔሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከመስከረም 2017 ጀምሮ

• ቪዮሪካ ዳንሲላ - የሮማንያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከጥር 2018 ጀምሮ

• አና ብራንቢች - የሰርቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከሰኔ 2017 ጀምሮ

• ሳይ ኢንግ-ዌን - የታይዋን ፕሬዝደንት፤ ከግንቦት 2016 ጀምሮ

አማርኛ፤ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት የሶስት ልጆች እናት የሆኑት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ያለግዜያቸው ሥልጣን ከለቀቁት ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ ነው መንበሩን የተረከቡት።

ምንም እንኳ የአዲሷ ፕሬዝደንት የመወሰን መብት ውሱን ቢሆንም ሃገሪቱ ውስጥ እየታየ ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።

ኢትዮጵያና ሩዋንዳ አፍሪቃ ውስጥ በርካታ ሴት የካቢኔ አባላትን በማካተት እየመሩ ይገኛሉ፤ በፕሬዝደንትነት ደግሞ ኢትዯጵያ ቁንጮ ሆናለች።

ወደፊት እንደ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ያሉ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ሴት መሪዎች እና ሳህለወርቅ ዘውዴን የመሰሉ ርዕሰ-ብሔራት በርክተው እናይ ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።