100 ያህል ታካሚዎችን ገድሏል የተባለው ጀርመናዊ ነርስ ጉዳይ ቁጣ ቀስቅሷል

100 ያህል ታካሚዎችን ገድሏል የተባለው ጀርመናዊ ነርስ ጉዳይ ቁጣ ቀስቅሷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጀርመናዊው ግለሰብ ነርስ ሳለ 100 የሚሆኑ በሽተኞችን አውቆ ገድሏል በሚል ክስ ተጠርጥሮ ለፍርድ ሊቀርብ መሆኑ ተሰምቷል።

ኒየልስ ሆግል የተባለው የ41 ዓመት ጎልማሳ በሰሜን ጀርመን በሰራባቸው ሁለት ሆስፒታሎች ውስጥ ከመጠን ያለፉና የመግደል አቅም ያላቸው መድሃኒቶችን ለሚከታተላቸው ታካሚዎች ይሰጥ ነበር ተብሏል።

መርማሪዎቹ እንደሚሉት ሰውዬው ይህንን የሚያደርገው በሞት አፋፍ ያደረሳቸውን ታካሚዎች መልሶ ነፍስ በመዝራት ከሥራ ባለደረቦቹ በልጦ ለመገኘት ሲል ነው።

ሰውዬው በሥራ ወቅት ሳለ ባጠፋው ሕይወት ሳቢያ ተፈርዶበት የዕድሜ ልክ እሥራት ላይ የሚገኝ ቢሆንም የ100 ሰዎች ነብስ እጅህ ላይ አጥፍተሀል የሚል ሌላ ክስ ተመሥርቶበታል።

ግሰለቡ የታካሚዎቹን ነብስ ያጠፋው በፈረንጆቹ ከ1999 - 2005 ባለው ጊዜ ነው ተብሏል።

የቢቢሲዋ ጄኒ ሂል ከበርሊን እንደምትለው የሰውዬው ጉዳይ የሃገሪቱን ጤና ሚኒስቴር ሁላ ሳይቀር ጭንቅ ውስጥ ከቷል፤ እንዴት ግለሰቡ ቁጥጥር አይደረግበትም የሚሉ ቁጣዎች ከዚያም ከዚህም መደመጣቸውን ተከትሎ።

ሰውዬው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የታዬ የሃገሪቱ 'ገዳይ' ሰው ይሆናል እየተባለ ነው።

መርማሪዎቹ «ኧረ እንደውም የገደላቸው ሰዎች ቁጥር ከዚህም ይልቃል፤ ሬሳቸው የተቃጠለ በመኖራቸው ማጣራት አልቻልንም እንጂ» ብለዋል።

ግለሰቡ የዛሬ 13 ዓመት የሃኪም ትዕዛዝ ያልተሰጠበት መርፌ አንድ በሽተኛን ሲወጋ ተገኝቶ ሰባት ዓመት ታሥሮ ተፈቷል።

የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ደግሞ በሁለት ግድያዎች ተጠርጥሮ ወንጀለኛ ሆኖ በመገኘቱ የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበታል።

«ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ» ያለው ግለሰቡ ፤ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግበት ተደርጎ ነው ሌሎች ተጨማሪ ነብሶች በእጁ ሳይጠፉ እንዳልቀሩ ሊጠረጠር የቻለው።

ይሰራባቸው በነበራቸው ሆስፒታሎች ግለሰቡ ተረኛ በሆነ ወቅት የሞት ቁጥር እንደሚጨምር ኋላ ላይ የተሠራ ጥናት አሳይቷል።