«ፕሬዝደንት 'ጥላቻ'፤ ከተማችንን ጥለው ይውጡ» የትራምፕ በተቃውሞ የታጀብ የፒትስበርግ ጉብኝት

«ፕሬዝደንት ጥላቻ ከተማችንን ጥለው ይውጡ» የትራምፕ በተቃውሞ የታጀብ የፒትስበርግ ጉብኝት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ እና ሜላኒያን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰብ አባላት በፒትስበርግ ተገኝተው ቅዳሜ ዕለት በተኩስ ለሞቱ አይሁዳውያን የሃዘን መልዕክልት አስተላልፈዋል።

ዕለተ ቅዳሜ ነበር አንድ ግለሰብ ወደ አይሁዳውያን የእምነት ሥፍራ በማቅናት 11 አማኞችን በጥይት የገደለው።

ቢሆንም የፕሬዝደንቱ ጉብኝት ጣጣ አላጣውም፤ ሁለት ሺህ ያህል ግለሰቦች ትራምፕን የሚቃወሙ መልዕክቶች በመያዝ ሰውዬውን መቀመጫ ነስተዋቸዋል።

ሟቾችን ለማሰብ በተዘጋጀው ሥፍራ ላይ አበባ ያኖሩት ትራምፕ ፀረ-ሴማዊ የሆኑ ጥቃቶች ሊቆሙ ይገባል ሲሉ አውግዘዋል።

ጉብኝቱ ላይ የተገኘችው የትራምፕ ሴት ልጅ ኢቫንካ ጃሬድ ኩሽነር የተባለውን አይሁድ ግለሰብ ካገባች በኋላ እምነቷን መቀየሯ ይታወቃል።

ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ የትራምፕ ተቃዋሚ ነበር የሚሉ መላ ምቶች ከዚያም ከዚህም ብቅ ማለት ጀምረዋል።

በከፋፋይ ንግግሮቻቸው የሚተቹት ትራምፕ ስደተኞችን እና ሙስሊሞችን በሚመለከት ባላቸው አቋም እየተብጠለጠሉ ይገኛል።

ዴሞክራቱ የፒትስበርግ ከንቲባ ቢል ፔዱቶ እና ሌሎች ስም ያላቸው አይሁዳውያን የትራምፕን ጉብኝት ተቃውመውታል።

«ትራምፕ የነጭ የበላይነትን የማያወግዙ ከሆነ ከተማችንን ሊጎበኙ አይገባም» ያሉ 70 ሺህ ያህል ግለሰቦች ፊርማ ያረፈበት ግልፅ ደብዳቤ ለትራምፕ ተፅፏል።

አበይት የሚባሉ የምክር ቤት ሰዎችም ከትራምፕ ጋር ወደ ፒትስበርግ ሄደው ጉብኝት እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ጥሪ ውድቅ አድርገውታል።

ጥቃቱን አድርሷል የተባለው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲሆን 29 ያህል ክሶች ይጠብቁታል።