አሜሪካዊው 'ጉደኛ ጋንግስተር' ጂሚ በልገር እሥር ቤት ውስጥ ተገደለ

'ጉደኛው ጋንግስተር' ባልገር እሥር ቤት ውስጥ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተወለደው በፈረንጆቹ 1929 ነው፤ የአሜሪካዊ እና የአይሪሽ ዝርያ ካላቸው ካቶሊክ ቤተሰቦች፤ ዕድገቱ ደግሞ ቦስተን ከተማ።

ቦስተን እያለ ነበር መኪና በመስረቅ የወንጀለኝነት ሕይወትን አንድ ብሎ የጀመረው፤ ለጥቆም ባንክ ወደ መዝረፍ ገባ።

ገና በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ነበር ቀለል ባለ ወንጀል ለእሥር የተዳረገው፤ እያለ እያለ ግን ከበድ ወዳሉ ወንጀሎች ዘለቀ።

በዝርፍያ እና ጠለፋ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ታዋቂ ወደሆነው የሳንፍራንሲስኮ ደሴት እሥር ቤት 'አልካትራዝ' ተላከ።

በነጭ ፀጉሩ ምክንያት 'ዋይቲ' በልገር እየተባለ የሚጠራው ይህ ወንጀለኛ 'አልካትራዝ' ከተሰኘው እሥር ቤት ጋር ፍቅር ከመውደቁ የተነሳ ከተፈታ በኋላ ጎብኚ መስሎ በመምጣት ፎቶ ተነስቷል።

ከግድያ እና ዝርፊያ ባለፈ በሰሜን አየርላንድ ላሉ አማፅያን የመሣሪያ አቅርቦት ለማድረግ ይጥር እንደነበር ይነገርለታል፤ ጂሚ 'ዋይቲ' በልገር።

ሁለት እንስቶችን በእጁ በማነቅ እንዲሁም አንድ ግለሰብ ለሰዓታት አሰቃይቶ ጭንቅላቱን በጥይት ማፍረስ፤ ጂሚ ባልገር ከሚታወቅባቸው እኩይ ተግባራት መካከል ናቸው።

ከአሜሪካው የወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት፤ ኤፍቢአይ ጋር አይንና ናጫ የነበረው በልገር በርካታ ጊዜ ታስሮ በርካታ ጊዜ አምልጧል።

በስተመጨረሻም 2011 ላይ ካሊፎርኒያ ውስጥ ከፍቅር ጓደኛው ካትሪን ጋር ተደብቆ ሳለ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ11 ግድያዎች እንዲሁም በሌሎች በርካታ ከባድ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው በልገር የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበት ጥብቅ በሆነው የፍሎሪዳ ማረሚያ ቤት ይገኝ ነበር።

ነገር ግን ባልታወቀ ምክንያት ወደ ምዕራብ ቨርጂኒያ እሥር ቤት በተዘዋወረ የመጀመሪያ ቀን በሌላ ታራሚ ተገድሎ ተገኝቷል።

ፖሊስ ጂሚ በልገር ለምን ከአንድ ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት ሊዛወር እንዳስፈለገ ያለው ነገር ባይኖርም የስነ-ልቡና አማካሪው ከሆነችው ሴት ጋር ግንኙነት ሳይጀምር እንዳልቀረ ምንጮች ሹክ ብለዋል።

የበልገር ሕይወት በርካታ የሆሊዉድ ፊልሞች መነሻ ሃሳብም ሆኖ አገልግሏል፤ 'ዘ ዲፓርትድ' የተሰኘውና ኦስካር ያሸነፈው ፊልም የሚጠቀስ ነው።

2015 ላይ ስለግለሰቡ ሕይወት ማወቅ የፈለጉ ተማሪዎች ደብዳቤ ፅፈውለት ሲመልስ «ሕይወቴ ባክኗል፤ በሞኝነት አሳልፌዋለሁ» ሲሉ ምላሽ ሰጥቶ እንደነበር አይዘነጋም፤ ጂሚ 'ዋይቲ' በልገር።